የዝንጀሮ ፈንጣጣ(Monkeypox)
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ሞንኪፖክስ በተባለ ቫይረስ የሚመጣ ተላላፊ በሽታ ሲሆን ይህ ቫይረስ ኦርቶፖክስ ከተባለ የቫይረስ ዝርያ ስር የሚመደብ የተሸፈነ ድርብ ክር ያለው ዲኤንኤ ቫይረስ ነው። ክላድ 1 እና ክላድ 2 የተሰኙ ሁለት ዋና ዋና የሞንኪ ፖክስ ዓይነቶች አሉ።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በዴንማርክ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1958 ዓ.ም ለምርመራ በተቀመጡ ዝንጀሮዎች ውስጥ ሲሆን በሰው ልጅ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው ደግሞ እ.ኤ.አ በ1970 ዓ.ም በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በዘጠኝ ወር ህጻን ልጅ ውስጥ ነው። እ.ኤ.አ. በ 1980 ዓ.ም የፈንጣጣ (Smallpox) መጥፋትን እና የፈንጣጣ ክትባት በዓለም አቀፍ ደረጃ ማብቃቱን ተከትሎ የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ቀስ በቀስ በመካከለኛው ፣ በምስራቅ እና በምዕራብ አፍሪካ እንዲሰራጭ ረድቶታል። ቀደም ሲል እንደሚታወሰው ከሁለት ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ በ2022-2023 ዓ.ም ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ተከስቶ የነበረ ሲሆን ይህም ወረርሽኝ የተከሰተው ክላድ 2b በሚባለው የሞንኪ ፖክስ ቫይረስ አይነት ነው።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ እንዴት ይተላለፋል ?
የቫይረሱ ተሸካሚ በእርግጥ ባይታወቅም እንደ ሽኮኮ እና ዝንጆሮ ያሉ የተልያዩ ትናንሽ አጥቢ እንስሳት ለበሽታው በከፍተኛ ደርጃ ተጋላጭ መሆናቸው ይነገራል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍበት ዋነኛ መንገድ በንክኪ ሲሆን ማለትም በበሽታው የተያዘን ሰው ቆዳ ወይንም ቁስል በምንነካበት ጊዜ በሽታው ይተላለፍብናል ይህም የሚከተሉትን ንክኪዎች ያጠቃልላል፦
- የ ፊት ለፊት ግንኙነት ማለትም በትንፋሽ
- የ ቆዳ ለቆዳ ንክኪ ፤ ይህም በሴት ብልት ወይም በ ፊንጢጣ የሚደረግ ወሲብን ያጠቃልላል
- በመሳሳም
- በአፍ በሚደረግ ወሲብ
- ከአፍ እና ከአፍንጫ በሚወጡ ጠብታዎች ሊተላለፍ ይችላል።
ከዚያም ቫይረሱ ወደ ሰውነታችን በተሰነጠቀ ቆዳ እና በውስጠኛው የአፋችን ፣ የፊንጢጣ ፣ የብልት እና የአይናችን ክፍል አማካኝነት ወይንም በመተንፈሻ አካላችን በኩል ይገባል።የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ አብሮን ከሚኖር የቤተሰብ አባል እና ከወሲብ አጋራችን ሊተላለፍብን ይችላል። ብዙ የወሲብ አጋር ያላቸው ሰዎች በዚህ በሽታ የመያዝ እድላቸውም ሰፊ ነው።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታም በበሽታው በተያዘ እንስሳ ከተነከስን ወይም ከተቧጨርን እንዲሁም በበሽታው የተያዘን እንስሳ በምናድንበት ፣ በምናርድበት ፣ ምግብ በምናዘጋጅበት እና በምንመገብበት ወቅት ሊተላለፍብን ይችላል። በቫይረሱ የተበከሉ ነገሮች እንደ አልባሳት፣ መርፌ የመሳሰሉትን በምንጠቀምበት እና ንቅሳት(tattoo) በምንሰራበትም ጊዜ በሽታው ሊተላለፍብን ይችላል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ምልክቶች ምን ምንድን ናቸው?
አብዛኛውን ጊዜ ለዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ከተጋለጥን በኋላ በሳምንት ውስጥ ምልክት ማሳየት እንጀምራለን ነገር ግን በዚ ብቻ የተወሰነ አይደለም ለቫይረሱ ከተጋለጥንበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እስከ 21ኛው ባሉት ቀናት ውስጥ ምልክት ልናሳይም እንችላለን።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ያለበት ሰው ከሚያሳያቸው ምልክቶች መካከል
- ሽፍታ
- ትኩሳት
- የጉሮሮ መቁሰል
- ራስ ምታት
- የጡንቻ ህመም
- የጀርባ ህመም
- ድካም
- የፍርንትት (Lymph node) ማበጥን ያጠቃልላል።
አንዳንድ ሰዎች በመጀመሪያ የሚያሳዩት ምልክት ሽፍታ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ከላይ ከጠቀስናቸው ምልክቶች መካከል አንዱ ቀድሞ ሊታይባቸው ይችላል። ሽፍታው የሚጀምረው ልክ እንደ ጠፍጣፋ ቁስል ሲሆን ይህም ቁስል ወደ ሚያሳክክ እና ሚቆጠቁጥ ውሃ ወደ ቋጠረ ቁስል ይቀየራል ከዚያም ይከስማል ። ቁስሉም በሚድንበት ጊዜ ጠባሳ ትቶ ሊያልፍ ይችላል።
አንዳንድ ሰዎች አንድ ወይም ጥቂት ሽፍታ ሲኖራቸው ሌሎች ደግሞ በመቶዎች ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ሽፍታዎች ይኖሯቸዋል። ይህም በማንኛውም የሰውነት ክፍል ላይ ሊታይ ይችላል ለምሳሌ
- በእጅ መዳፍ እና በእግር መርገጫ
- በፊት ፣ በአፍ እና በጉሮሮ
- በብሽሽት እና በብልት አካባቢ
- በፊንጢጣ እና በመሳሰሉት ላይ ቁስሉ ሊወጣብን ይችላል።
ሽፍታው ከፊታችን በመጀመር ወደ ሌላው የሰውነታችን ክፍል ይሰራጫል ወደ እጆቻችን መዳፍ እና የእግራችን መረገጫ ይደርሳል የተለያዩ ደረጃዎችንም በማለፍ ከ 2-4 ሳምንታት በኋላ መድረቅ ይጀምራል። የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ቁስላቸው ድኖ አዲስ ቆዳ እስኪፈጠር ድረስ በሽታውን ወደ ሌሎች ሰዎች ያስተላልፋሉ።
አንዳንድ ሰዎች ምንም አይነት ምልክት ሳያሳዩ በሽታውን ሊያስተላልፉም ይችላሉ።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ያለበት ሰው በጣም ሊታመም ይችላል። ለምሳሌ ቆዳው በባክቴርያ ሊበከል ይችላል ይህም መግል እንዲፈጠር ወይም ከባድ የቆዳ ጉዳት እንዲደርስበት ያደርጋል። እንደ የሳንባ ምች ፣ ለአይን ብርሃን ማጣት የሚዳርግ የአይን ኢንፈክሽን ፣ ለመዋጥ መቸገር ወይም በምንውጥበት ግዜ ህመም መኖር፣ ትውከት እና ተቅማጥ ፣ የደም ኢንፌክሽን(ሴፕሲስ) ፣ የአንጎል ብግነት(ኢንሰፍላይትስ) ፣ የልብ ጡንቻ ብግነት(ማዮካርዳይትስ) ፣ የፊንጢጣ ፣ የብልት እና የሽንት ቱባ ኢንፌክሽን የመሳሰሉትን የጎንዮሽ ችግርም ሊያስከትል እና ለሞት ሊዳርግም ይችላል።
ህፃናት ፣ እርጉዝ ሴቶች እና በሽታ የመከላከል አቅማቸው የደከመ ሰዎች ለምሳሌ ኤቻይቪ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ሰዎች ለዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ እና ለከባድ የጎንዮሽ ጉዳት የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ምርመራ
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታን ከሌሎች ተመሳሳይ በሽታወች እንደ ጉድፍ ፣ ኩፍኝ ፣ የባክቴርያ የቆዳ ኢንፌክሽን ፣ እከክ፣ ሄርፒስ ፣ቂጥኝ ፣ በግብረ ስጋ ግኑኝነት ከሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች እና ከመሳሰሉት በሽታዎች ለመለየት አዳጋች ሊሆን ይችላል ስለዚህም የዝንጀሮን ፈንጣጣ በሽታን በቶሎ ለማግኘት እና ስርጭቱን ለመግታት ምርመራ ያስፈልጋል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታን ለመለየት ተመራጭ የሆነው የላብራቶርይ ምርመራ ፖሊሜሬስ ቼን ሪያክሽን (ፒሲአር) የተባለው ምርመራ ነው።ይህም ምርመራ ከሽፍታው ናሙና ማለትም ከቁስሉ የሚወጣን ፈሳሽ ወይንም የደረቀ ቅርፊት በመውሰድ የሚሰራ ምርመራ ሲሆን የቫይረሱ ዲ ኤን ኤ መኖሩን ይለይልናል። በቆዳችን ላይ ምንም አይነት ሽፍታ ከለለ ናሙናውን ከ ጉሮሮ ወይም ከፊንጢጣ በመውሰድ ምርመራው ሊሰራልን ይችላል። የፀረ እንግዳ አካል (antibody) ምርመራ በኦርቶፖክስ ዝርያ ስር ካሉት ቫይረሶች መካከል የትኛው ቫይረስ መሆኑን ስለማይለይልን ይህን ምርመራ ማድረግ ብዙም ጥቅም የለውም።
በምርመራ ወቅት የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ የተገኘባቸው አዋቂዎችን እና እንዳስፈላጊነቱ ህፃናትን ለ ኤቻይቪ በሽታ መመርመር ተገቢ ነው።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ሕክምና እና ክትባት
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ሕክምና ዋናው ግብ ሽፍታውን ማከም ፣ ህመምን መቀነስ እና በበሽታው ምክንያት የሚመጡ የጎንዮሽ ጉዳቶችን መከላከል ነው። ስለዚህም በበሽታው ለተያዙ ሰዎች ቶሎ እንክብካቤ መጀመር አስፈላጊ ነው።
በበሽታው ከመያዛችን በፊት የዝንጀሮ ፈንጣጣ(mpox) ክትባትን መውሰድ በበሽታው እንዳንያዝ ይረዳናል። ይህም በከፍተኛ ደረጃ ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ (high risk) ሰዎች እንዲሰጥ ይመከራል በተለይም በወረርሽኝ ወቅት።
ለዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸው ሰዎች የሚከተሉትን ያጠቃልላል፡-
- የጤና ባለሞያዎች እና በበሽታ የተያዘውን ሰው የሚንከባከቡ ሰዎች
- ህፃናትን ጨምሮ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ካለው ሰው ጋር በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ወይም በቅርብ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ሰዎች
- ብዙ የወሲብ ጓደኛ ያላቸው ሰዎች ይህም ከወንዶች ጋር የግብረ ስጋ ግኑኝነት የሚፈፅሙ ወንዶችን ይጨምራል
- ሴተኛ አዳሪዎች እና ደንበኞቻቸው በበሽታው የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ ነው።
ክትባቱም በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ግኑኝነት ለነበራቸው ሰዎችም ሊሰጥ ይችላል(post exposure prophylaxis)። ይህም የዝንጀሮ ፈንጣጣ ካለበት ሰው ጋር ከተገናኙ በ 4 ቀናት ውስጥ ክትባቱ ሊሰጣቸው ይገባል። የተጋለጠው ሰው ምንም አይነት ምልክት ካላሳየ ግን ክትባቱ እስከ 14 ቀን ድረስ ሊሰጥ ይችላል።
አንዳንድ አገሮች አንዳንድ የፀረ ቫይረስ መድሃኒቶች በአደጋ ጊዜ እንዲሰጡ ፈቅደዋል እነዚህም መድሃኒቶች በክሊኒካዊ ሙከራዎች እየተገመገሙ ይገኛሉ።ይሁን እንጂ እነዚህ የፀረ ቫይረስ መድሃኒቶች በዝንጀሮ ፈንጣጣ ሕክምና ላይ የተረጋገጠ ውጤታማነት እስካሁን አልታየባቸውም።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ የተገኘባቸው ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ያለ ሰዎች ኤአርቲ(ART) የኤችአይቪ መድሃኒት መውሰዳቸውን መቀጠል አለባቸው።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ላለባቸው ሰዎች የሚደረግ እንክብካቤ
አብዛኞቹ የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ከ2-4 ባሉት ሳምንታት ውስጥ ከበሽታው ያገግማሉ። ከየዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ምልክቶች ለማገገም እና በሽታውን ወደሌሎች እንዳናስተላልፍ እንዲረዱን ማድረግ ያለብን ነገሮች የሚከተሉት ናቸው
- የጤና ባለሞያ ማማከር ይኖርብናል
- ከቤት ሳንወጣ አንድ ክፍል ውስጥ ብቻችን መሆን አለብን ይህም ወደ ሌሎች እንዳናስተላልፍ ይረዳናል። ከተቻለ የምንቀመጥበት ክፍል በደንብ አየር የሚዘዋወርበት ቢሆን ይመረጣል
- በተቻለ መጠን እጃችንን በውሃ እና በሳሙና ቶልቶሎ መታጠብ ወይም በሳኒታይዘር ማፅዳት በተለይም ቆዳችን ላይ የወጣውን ሽፍታ ከመንካታችን በፊት እና ከነካን በኋላ መታጠብ ይኖርብናል
- ማስክ ማድረግ እና ከሰዎች ጋር በምንሆንበት ጊዜ ቆዳችን ላይ ያለውን ሽፍታ መሸፈን አለብን ይህንንም ሽፍታው እስኪድንልን ድረስ እናደርጋለን
- ቆዳችን ምንም አይነት እርጥበት እንዳይኖረው እና ደረቅ እንዲሆን ማድረግ አለብን እንዲሁም ቆዳችንን ሳንሸፍን ክፍት ማድረግ ይኖርብናል (ከሌላ ሰው ጋር ካልሆንን በስተቀር)
- በጋራ ቦታዎች ውስጥ ያሉ እቃዎችን ከመንካት መቆጠብ እና እነዚህን ቦታዎች በተደጋጋሚ ማፅዳት አለብን
- አፋችን ውስጥ ቁስል ካለ አፋችንን በጨው ውሃ መጉመጥመጥ
- ሰውነታችንን በቤኪንግ ሶዳ ወይም በእንግሊዝ ጨው በሞቀ ውሃ መታጠብ ይህም ለሰውነት ቁስሉ ይረዳናል
- ህመምን ለማስታገስ እንደ ፓራሴታሞል(paracetamol) እና አይቦፕሮፊን (ibuprofen) ያሉ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን መውሰድ እንችላለን።
ማድረግ የሌሉብን ነገሮች ደግሞ የሚከተሉትን ይመስላሉ ፡-
- ውሃ የቋጠሩትን ሽፍታዎች ማፈንዳት እና ቁስላችንን ማከክ ምክንያቱም ይህን ማድረግ ቁስሉ ቶሎ እንዳይድን፣ በባክቴሪያ እንዲበከል እና ሽፍታውን ወደ ሌላ የሰውነታችን ክፍል እንድናስተላልፍ ያደርጋል
- ቁስል ያለባቸው የሰውነት ቦታዎች አካባቢ መላጨት ይህም ወደ ሌላ የሰውነታችን ክፍል ሽፍታው እንዲሰራጭ ስለሚያደርግ ፈጽመን ማድረግ የለብንም።
በግብረ ስጋ ግኑኝነት ወቅት ኮንዶም መጠቀም የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ የመተላለፍ እድልን እንዲቀንስ ቢያደርግም በቆዳ እና ቆዳ ወይንም በአፍ እና ቆዳ ያለውን ንክኪ እና የበሽታውን መተላለፍን ግን አይከላከልልንም። ስለዚህ በበሽታው ወቅጥ ከግብረ ስጋ ግንኙነት ብንቆጠብ ይመከራል። ከበሽታው ካገገምን በኋላም ቢያንስ ለ 12 ሳምንታት(3 ወራት) በግብረ ስጋ ግኑኝነት ጊዜ ኮንዶም መጠቀም ይኖርብናል። የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ካለበት ሰው ጋር የቅርብ ግኑኝነት የነበረው ሰውም ቢያንስ ለ 21 ቀናት(3 ሳምንታት) ከማንኛውም አይነት የወሲብ ግኑኝነት መቆጠብ አለበት።
የጤና ባለሞያዎችም የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ያለበትን ሰው በሚንከባከቡበት ጊዜ ተገቢውን የግል መከላከያ ትጥቅ እንደ ጓንት፣ጋውን፣የአይን እና የመተንፈሻ አካል መከላከያ የመሳሰሉትን በማድረግ እራሳቸውን ከበሽታው መከላከል ይኖርባቸዋል።




