ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ከባድ የአእምሮ መታወክ
ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ከባድ የአእምሮ መታወክ (Postpartum psychosis) አልፎ አልፎ የሚያጋጥም ነገር ግን አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ የሚሻ የአእምሮ ጤና እክል ነው። ይህ ሁኔታ እናቲቱ ከእውነታው ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት እንዲቋረጥ ስለሚያደርግ፣ በራሷ ወይም በልጇ ላይ ጉዳት የማድረስና ራሷን የማጥፋት ከፍተኛ ሥጋት ያሳድራል። በመሆኑም ሁኔታው አስቸኳይ ሕክምና የሚያስፈልገው የአእምሮ ጤና እክል (Mental health emergency) ነው።
ይህ እክል በቅርቡ የወለደች ማንኛዋንም እናት ሊያጠቃ ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ እናቲቱ በወለደች በጥቂት ቀናት ውስጥ የሚጀምር ሲሆን እስከ 6 ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥም ሊከሰት ይችላል።
ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ከባድ የአእምሮ መታወክ በግምት ከ1,000 እናቶች አንዷን ሊያጠቃ ይችላል።
ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ከባድ የአእምሮ መታወክ ምልክቶች ምንድን ናቸው?
ይህ የአእምሮ ሕመም በአስተሳሰብ፣ በስሜት፣ በባሕርይና እውነታን የመገንዘብ አቅም ላይ ፈጣንና ከባድ ለውጦችን ያስከትላል።
የዚህ እክል ሁለቱ ዋና ዋና ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው
- የሌሉ ነገሮችን ማየት ወይም ድምፆች መስማት (Hallucinations)
በእውኑ የሌሉ ነገሮችን ማየት፣ መስማት ወይም የሌለ ስሜት መሰማት ሲሆን እናቲቱ እነዚህ ነገሮች እውነተኛ እንደሆኑ አጥብቃ ታምናለች።
- እውነት ያልሆኑ ነገሮችን በጽኑ ማመን (Delusions)
ነገሮች እውነት እንዳልሆኑ ግልጽ ማስረጃ ቢኖርም የተሳሳቱ እምነቶችን አጥብቆ መያዝ ፤ ለምሳሌ፦ አንድ ሰው ሊጎዳት እንደሆነ ማመን፣ የሆነ አካል እየተቆጣጠራት እንደሆነ ማሰብ ወይም ልጇ እንዳልተወለደ ጭራሹንም ነፍሰ ጡር እንዳልነበረች ማመን።
ከዚህም በተጨማሪ የሚከተሉት ምልክቶች ሊታይባት ይችላል
- ከፍተኛ የስሜትና የባሕርይ መዋዠቅ (ከፍተኛ የደስታ ወይም የመነቃቃት ስሜት (Mania) ማሳየት ከዚያም ወደ ጥልቅ ሐዘን እና ድብርት መግባት)
- የመደናገር ወይም ግራ የመጋባት ስሜት
- ለመረዳት የሚያስቸግር ንግግር ወይም ያልተለመደ ባሕርይ ማሳየት
- ከባድ የእንቅልፍ ችግሮች
- በትንሽ ነገር መቆጣት፣ መነጫነጭ ወይም ስሜታዊ መሆን
- ከራስ የመነጠል ስሜት (Depersonalization) እና እናቲቱ ከራሷ አካል ውጭ እንደሆነች አድርጋ ማሰብ
- ቀደም ሲል ደስታ ከሚሰጣት ነገሮች ደስታ አለማግኘት ወይም ነገሮችን ለማድረ ፍላጎት ማጣት
- የምግብ ፍላጎት ማጣት ወይም መለዋወጥ
- ከፍተኛ የበደለኛነት፣ የፍርሃት ወይም የድንጋጤ ስሜት መሰማት
- ሙሉ በሙሉ ዝም ማለት፣ እንቅስቃሴ መቀነስ ወይም ለአካባቢ ምላሽ አለመስጠት (Catatonia)
- ራስ ላይ ጉዳት የማድረስ ወይም ራስን የማጥፋት ሀሳቦች መኖር
- በአዲስ በተወለደው ህፃን ወይም በሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት የማድረስ ፍላጎት ወይም ሀሳብ መኖር።
ለሕመሙ የመጋለጥ ዕድልን የሚጨምሩ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
ሐኪሞች ለዚህ እክል መንስኤ የሚሆኑትን ነገሮች በእርግጠኝነት ባያውቁም የሚከተሉት ሁኔታዎች ግን ለአደጋው መከሰት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይገልጻሉ
- ቀደም ሲል እንደ ከፍተኛ የስሜት መዋዠቅ (Bipolar disorder)፣ ድባቴ ወይም የስኪዞፈሪንያ ሕመም (Schizophrenia-spectrum) ያሉ ችግሮች ከነበሩ
- የመጀመሪያ ወሊድ ከሆነ
- ቀደም ሲል በዚህ ሕመም ተጠቅተው ከነበረ
- በቤተሰብ ውስጥ ተመሳሳይ የአእምሮ ጤና ሕመም ካለ
- እንቅልፍ ማጣት ወይም ከፍተኛ የእንቅልፍ መዛባት
- ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ከፍተኛ የሆርሞን መዋዠቅ
- እንደ የታይሮይድ ችግር፣ የቪታሚን እጥረት፣ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት (Preeclampsia) እና የበሽታ መከላከል ሥርዓት መዛባት (autoimmune diseases) ያሉ የጤና እክሎች መኖር
ከወሊድ በኋላ ለሚከሰት ከባድ የአእምሮ መታወክ የሚደረግ ምርመራ ምን ይመስላል?
ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ከባድ የአእምሮ መታወክ የሚመረመረው የእናቲቱን ምልክቶች፣ ባሕርይ፣ የአእምሮ ሁኔታና አጠቃላይ ጤና በመገምገም ነው። በተጨማሪም ሐኪሞች ሌሎች ተመሳሳይ ምልክት የሚያሳዩ ሕመሞችን ለመለየት የአካልና የነርቭ ምርመራዎችን ሊያደርጉ ይችላሉ።
ተመሳሳይ ምልክቶች ሊያስከትሉ የሚችሉ ሌሎች ሁኔታዎችን ለመለየት የሚከተሉት ተጨማሪ ምርመራዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ ፦
- የደም እና የሽንት ምርመራዎች
ኢንፌክሽኖችን፣ የኤሌክትሮላይት ወይም የሆርሞን መዛባትን፣ የቪታሚንና የማዕድናት እጥረትን እንዲሁም የኩላሊት ወይም የጉበት ችግሮችን ለመለየት ይረዳሉ።
- የአእምሮ ምስል ምርመራ (Brain imaging)
የነርቭ ወይም የአንጎል መዋቅራዊ ችግሮችን ለመለየት ሐኪሞች የሲቲ ስካን (CT scan) ወይም የኤምአርአይ (MRI) ምርመራዎችን ሊያዝዙ ይችላሉ።
- የአእምሮ ጤና ግምገማ
እንደ ሳይኮሲስ፣ ድባቴ ወይም የስሜት መነቃቃት (mania) ያሉ ምልክቶችን ለመገምገም መጠይቆች እና ክሊኒካዊ ግምገማዎች ሊደረጉ ይችላሉ።
በመጨረሻም ሐኪሞች የእናቲቱን ምልክቶች፣ የሕክምና ታሪክና የምርመራ ውጤቶች በጥንቃቄ ግምት ውስጥ በማስገባት ሁኔታው ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ከባድ የአእምሮ ሕመም መሆኑን ይለያሉ።
ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ከባድ የአእምሮ መታወክ እንዴት ይታከማል?
ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ከባድ የአእምሮ መታወክ ተገቢው ሕክምና ከተደረገለት ሙሉ በሙሉ መዳን የሚችል እክል ነው። እናቲቱ በቅርብ ክትትል እንድታገኝና ደኅንነቷ እንዲጠበቅ ሕክምናው አብዛኛውን ጊዜ በሆስፒታል ተኝቶ መታከምን ይፈልጋል።
ዋና ዋና የሕክምና አማራጮች ፦
- የመድኃኒት ሕክምና
ሳይኮሲስን፣ ከባድ የስሜት መለዋወጥንና ተያያዥ ምልክቶችን ለመቆጣጠር የፀረ-ሳይኮሲስ (Antipsychotics)፣ ቤንዞዲያዜፒን (Benzodiazepines/CNS Depressants) እንዲሁም እንደ ሊቲየም (Lithium) ያሉ የስሜት ማረጋጊያ (Mood Stabilizers) መድኃኒቶች ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ።
- የኤሌክትሪክ ንዝረት ሕክምና (Electroconvulsive Therapy - ECT)
ምልክቶቹ ከባድ በሚሆኑበት ወይም ፈጣን ለውጥ በሚያስፈልግበት ወቅት የኤሌክትሪክ ንዝረት ሕክምና (ECT) ሊመከር ይችላል። ሕክምናው ሙሉ ማደንዘዣ (general anesthesia) ከተሰጠ በኃላ የሚከናወን ሲሆን የአእምሮ ተግባርን ለማነቃቃት ተገቢው ቁጥጥር የተደረገለት የኤሌክትሪክ ንዝረትን ይጠቀማል። ይህም ቀላል የሆነ መናድ (seizure) እንዲከሰት ያደርጋል። የመናዱም ተፅዕኖ የአእምሮ እንቅስቃሴን በመለወጥ ከወሊድ በኋላ የሚከሰተውን ከባድ የአእምሮ ሕመም (PPP) ምልክቶች እንዲቀንሱ ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲድኑ ይረዳል።
የሚሰጡት የሕክምና አማራጮች እንደ እናቲቱ ምልክቶች፣ የሕክምና ታሪክና ለሕክምናው የምትሰጠውን ምላሽ መሠረት በማድረግ ይወሰናሉ። ሐኪሞችም በሕክምናው ሂደት ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችንና ሌሎች ሁኔታዎችን በቅርብ ይከታተላሉ።
ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ከባድ የአእምሮ መታወክ በቤት ውስጥ ሊታከም ይችላል?
ይህንን ሕመም እናቲቱ ወይም ቤተሰቦቿ በቤት ውስጥ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ሊያክሙት አይችሉም። ሁኔታው እናቲቱ እውነታውን የመለየት አቅሟን ስለሚነካው ሕመሙ እንዳለባት ላታውቅ ትችላለች። ስለዚህ በቅርቧ ያሉ ወዳጅ ዘመዶቿ የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ቀድመው በማስተዋል በፍጥነት አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ እንድታገኝ ሊረዷት ይገባል።
ከሕመሙ ለማገገም ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?
ቀደም ብሎ በሚደረግ ሕክምና አብዛኞቹ እናቶች በስድስት ሳምንታት ውስጥ ማገገም ይጀምራሉ። ተገቢው ሕክምና ካልተደረገ ግን ምልክቶቹ ረዘም ላለ ጊዜ ሊቆዩና ይበልጥ ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ።
እንዲሁም ይህ ሕመም የሚያጋጥማቸው እናቶች ለከፍተኛ የስሜት መዋዠቅ ሕመም (Bipolar Disorder) የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ሊሆን ስለሚችል፣ ካገገሙ በኋላም ቀጣይነት ያለው የሕክምና ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ሕመሙን መከላከል ይቻላል?
ከወሊድ በኋላ የሚከሰተውን ይህንን ከባድ የአእምሮ መታወክ ሕመም ሙሉ በሙሉ ለመከላከል የሚያስችል የተረጋገጠ መንገድ የለም። ነገር ግን ቀደም ሲል ይህ ሕመም አጋጥሟቸው የነበሩ ወይም ከፍተኛ የስሜት መዋዠቅ ህመም (Bipolar Disorder) ያለባቸው እናቶች ላይ በድጋሚ የመከሰት ዕድሉን መቀነስ ይቻላል። በመሆኑም ለእነዚህ እናቶች እንደ ሊቲየም (Lithium) ያሉ የመከላከያ መድኃኒቶችን መስጠት ሊመከር ይችላል።




