የሴት ልጅ ድንግልና (Hymen) ፡ ሳይንሳዊ እውነታዎችና የተሳሳቱ አመለካከቶች
«ድንግልናዋ ተወሰደ» ወይም «ድንግልናዋ ፈረሰ» የሚሉ አባባሎችን በተደጋጋሚ ሰምተን እናውቃለን። ብዙዎቻችን ስለ ድንግልና ሽፋን (Hymen) ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማነውም በእነዚህ ልማዳዊ አነጋገሮች በኩል ነው። ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ በዚህ ርዕስ ዙሪያ ሰፊ ግራ መጋባትና የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ይስተዋላሉ። በዚህ ጽሑፍ የድንግልና ሽፋን በትክክል ምን እንደሆነ፣ ዓይነቶቹንና ተግባሩን በሳይንሳዊ እውነታዎች ተንተርሰን እንመለከታለን።
የድንግልና ሽፋን (Hymen) ምንድን ነው?
የድንግልና ምልክት ወይም ሽፋን (Hymen) በሴት ብልት መግቢያ አካባቢ የሚገኝ ቀጭንና የመለጠጥ ባሕሪ ያለው ተፈጥሯዊ ሽፋን ነው። ይህ ሽፋን በማኅፀን ውስጥ በፅንስ ዕድገት ወቅት የሴት ብልት (ከረቤዛ) በሚፈጠርበት ጊዜ የሚቀር ተፈጥሯዊ ኅብረ-ሕዋስ ነው።
የድንግልና ሽፋን ቅርጹ፣ መጠኑ እና ውፍረቱ በተፈጥሮ ከሴት ወደ ሴት ይለያያል። በአብዛኛዎቹ ሴቶች ላይ በብልት መግቢያ ዙሪያ እንደ ቀለበት ወይም ግማሽ ጨረቃ ቅርጽ ሆኖ የሚገኝ ሲሆን የወር አበባ ደም ያለ እንቅፋት ወደ ውጭ እንዲወጣ የሚያስችል ተፈጥሯዊ ክፍተት (ቀዳዳ) አለው። ሴት ልጅ ለአቅመ ሔዋን ስትደርስ (በጉርምስና ወቅት) በሰውነቷ ውስጥ የኢስትሮጅን (Estrogen) ሆርሞን መጠን ስለሚጨምር፣ ይህ ሽፋን በልጅነት ጊዜ ከነበረው ይበልጥ ወፈር ያለና በቀላሉ የመለጠጥ ባሕሪ ያለው ይሆናል።
የድንግልና ሽፋን (Hymen) ምን ጥቅም ይሰጣል?
የድንግልና ሽፋን በመራቢያ አካላት ሥርዓት ውስጥ በግልጽ የታወቀ ፊዚዮሎጂያዊ ተግባር የለውም። አንዳንድ ተመራማሪዎች በተለይ በሕፃንነት ዕድሜ ባዕድ ነገሮች ወይም ባክቴሪያዎች ወደ ውስጥ እንዳይገቡ መጠነኛ ከለላ ሊሰጥ ይችላል የሚል ግምት ቢያቀርቡም እስካሁን በሳይንስ የተረጋገጠ ግልጽ ጥቅም ግን የለውም።
አምስቱ ተፈጥሯዊ የድንግልና ሽፋን ዓይነቶች
የድንግልና ሽፋን ቅርጽ የሚወሰነው ገና በፅንስ ዕድገት ወቅት በመሆኑ፣ በራስ ጥረት መቆጣጠርም ሆነ መለወጥ አይቻልም። አብዛኞቹ የሽፋኑ ተፈጥሯዊ ልዩነቶች ፍጹም ጤናማ ቢሆኑም፣ የተወሰኑት ግን የወር አበባ ደም በነፃነት እንዳይፈስ እክል ሊፈጥሩ ይችላሉ፦
1. ቀለበት መሰል ወይም ግማሽ ጨረቃ ቅርጽ ያለው (Annular or Crescent-Shaped Hymen)
በጣም የተለመዱና ጤናማ ቅርጾች ናቸው። የወር አበባ ደም ያለ ምንም ችግር እንዲፈስ ያስችላሉ።
2. ወንፊት መሰል ሽፋን (Cribriform Hymen)
ከአንድ ትልቅ ቀዳዳ ይልቅ በርካታ ጥቃቅን ቀዳዳዎች ይኖሩታል። የወር አበባ ደም ቢያልፍም እንደ ታምፖን (Tampon) ያሉ የንፅህና መጠበቂያዎችን ወደ ውስጥ ለማስገባት ግን አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።
3. ሙሉ በሙሉ የተዘጋ ሽፋን (Imperforate Hymen)
የብልት መግቢያን ሙሉ በሙሉ በመዝጋት የወር አበባ ደም እንዳይወጣ የሚያግድ አልፎ አልፎ የሚከሰት እክል ነው። ልጃገረዶች የወር አበባ ማየት ሲጀምሩ ደሙ ከሽፋኑ ጀርባ ስለሚጠራቀም በታችኛው ሆድና በዳሌ አካባቢ ከባድ ሕመም ያስከትላል።
4. በጣም ትንሽ ቀዳዳ ያለው ሽፋን (Microperforate Hymen)
የሴት ብልት መግቢያን ሙሉ በሙሉ ለመዝጋት በተቃረበ መልኩ የሚሸፍንና እጅግ ጠባብ ቀዳዳ ብቻ ያለው የሽፋን ዓይነት ነው። ብዙውን ጊዜ የወር አበባ ደም በዚህ ጠባብ ቀዳዳ በኩል ማለፍ ቢችልም፣ ታምፖን (Tampon) ማስገባትንና ማውጣትን ግን እጅግ አስቸጋሪ ያደርገዋል።
5. የተከፈለ ሽፋን (Septate Hymen)
በመግቢያው ላይ ተጨማሪ የኅብረ-ሕዋስ ገመድ (Band) በመኖሩ ቀዳዳውን ወደ ሁለት ትናንሽ ክፍሎች ይከፍለዋል። ይህም ታምፖን ለመጠቀም አዳጋች ያደርገዋል።
በድንግልና ዙሪያ ያሉ 5 የተሳሳቱ አመለካከቶች
በብዙ ሰዎች ዘንድ ስለ ድንግልና በርካታ የተሳሳቱ አመለካከቶች አሉ። ከእነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦
- ሁሉም ሴቶች የድንግልና ምልክት አላቸው
ይህ ፍጹም የተሳሳተ ግንዛቤ ነው። አብዛኞቹ ሴቶች ሽፋኑ ኖሯቸው የሚወለዱ ቢሆንም፣ የተወሰኑ ሴቶች ግን እጅግ አነስተኛ ሽፋን ኖሯቸው ወይም ምንም ዓይነት ሽፋን ሳይኖራቸው ይወለዳሉ። ይህም በተፈጥሯዊ የሰውነት አወቃቀር (Anatomy) ላይ የሚታይ ተፈጥሯዊ ልዩነት ነው።
- ሽፋኑ የሴት ብልት መግቢያን ሙሉ በሙሉ ይዘጋል
በአብዛኛው ሁኔታ ሽፋኑ የወር አበባ ደም ያለ እንቅፋት እንዲወጣ የሚያስችል ተፈጥሯዊ ክፍተት አለው። አልፎ አልፎ ግን መግቢያውን ሙሉ በሙሉ ሊዘጋ (Imperforate hymen) ወይም በጣም ጠባብ ክፍተት ሊኖረው ይችላል። ይህም ቀላል የቀዶ ሕክምና ያስፈልገዋል።
- የድንግልና ምልክት የሴቷን ድንግልና ያረጋግጣል
ይህ ስለ ድንግልና ከሚነገሩ የተሳሳቱ አመለካከቶች ዋነኛው ነው።
ብዙ ሰዎች ያልተቀደደ ሽፋን መኖሩ አንዲት ሴት ቀደም ሲል የግብረ ስጋ ግንኙነት አድርጋ እንደማታውቅ ያረጋግጣል ብለው ያምናሉ። በዚህ ማኅበራዊ ጫና ምክንያት በርካታ ሴቶች ሽፋኑን መልሶ ለመስፋት የሚደረገውን ቀዶ ሕክምና (Hymenoplasty) እንዲያደርጉ ይገደዳሉ።
ነገር ግን ሽፋኑ በተፈጥሮ የተለያየ ከመሆኑም ባሻገር በሌሎች በርካታ ምክንያቶች ሊለጠጥ ስለሚችል። የሕክምና ባለሙያዎች እንኳን ምርመራ በማድረግ አንዲት ሴት ከዚህ ቀደም የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ማድረጓን ወይም አለማድረጓን በእርግጠኝነት ማረጋገጥ አይችሉም።
- በመጀመሪያ ግንኙነት ወቅት ሁሉም ሴት የግድ ደም ይፈሳቸዋል
ብዙ ሰዎች በመጀመሪያው የግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት ደም ይፈሳል ብለው ይጠብቃሉ፤ ይህ ግን ለሁሉም ሴቶች እውነት አይደለም።
የድንግልና ምልክት የመለጠጥ ባሕሪ ያለው በመሆኑ ሳይቀደድና ደም ሳይፈስ ሊለጠጥ ይችላል። በተጨማሪም ሽፋኑ አነስተኛ የደም ሥሮች ያሉት በመሆኑ ደም መፍሰስ በሁሉም ሴቶች ላይ የግድ የሚከሰት ነገር አይደለም።
- ሽፋኑን በቀላሉ በዓይን ማየት ወይም በእጅ መዳሰስ ይቻላል
ሽፋኑ በሴት ብልት መግቢያ ውስጠኛ ክፍል የሚገኝ በመሆኑ ስለ ሰውነት አወቃቀር በቂ ዕውቀትና የሕክምና መሣሪያ ሳይኖር በውጫዊ እይታ በቀላሉ ለይቶ ማወቅ አይቻልም።
ከዚህም በተጨማሪ የወሲብ አጋር በግንኙነት ወቅት በመዳሰስ ብቻ አንዲት ሴት የድንግልና ምልክት ያላት መሆኑን በእርግጠኝነት መለየት አይችልም።
ሽፋኑ ከግብረ-ሥጋ ግንኙነት ውጭ በምን ምክንያቶች ሊለጠጥ ወይም ሊቀደድ ይችላል?
አንዲት ሴት የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ከመጀመሯ በፊት በሚከተሉት የተለመዱ ምክንያቶች ሽፋኑ ሊለጠጥ ወይም ሊቀደድ ይችላል፦
- ብስክሌት ወይም ፈረስ በመጋለብ፤
- ጂምናስቲክና ከባድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ፤
- ራስን በራስ በማርካት (Masturbation)፤
- እንደ ታምፖን (Tampons) ወይም የወር አበባ ጽዋ ያሉ የንፅህና መጠበቂያዎችን ወደ ብልት በማስገባት፤
- የማኅፀንና የዳሌ ምርመራዎች ወይም የማኅፀን በር ካንሰር ቅድመ ምርመራ (Pap test) በሚደረግበት ወቅት።
የእያንዳንዷ ሴት ተሞክሮ የተለያየ ነው፤ አንዳንዶች ሽፋኑ ሲለጠጥ ወይም ሲቀደድ መጠነኛ ሕመምና አነስተኛ የደም መፍሰስ ሲያስተውሉ ሌሎች ደግሞ ምንም ዓይነት ምልክት ሳይታይባቸው መቼና እንዴት እንደተቀደደ እንኳ ላያውቁ ይችላሉ።
ከተቀደደ በኋላ ተመልሶ ያድጋል?
የድንግልና ሽፋን በፅንስ ዕድገት ወቅት የሚፈጠር ኅብረ-ሕዋስ በመሆኑ አንዴ ከተለጠጠ ወይም ከተቀደደ በኋላ ተመልሶ ወደ ቀድሞው ቅርጹና ይዞታው አያድግም። ይሁን እንጂ እንደ ማንኛውም የሰውነት ቆዳ ኅብረ-ሕዋስ ጥቃቅን መሰንጠቆች ሲያጋጥሙት በጊዜ ሂደት ይድናል፤ በዚህም ምክንያት ሽፋኑ ሙሉ በሙሉ ከመጥፋት ይልቅ በብልት መግቢያ ዙሪያ ትናንሽ ተፈጥሯዊ እጥፋቶች ሆኖ ይቀጥላል።
ምርመራና ሕክምና የሚያስፈልገው መቼ ነው?
አብዛኛዎቹ የድንግልና ሽፋን ዓይነቶች ምንም ዓይነት ሕክምና አያስፈልጋቸውም። ይሁን እንጂ የወር አበባ ደም እንዳይፈስ የሚከለክል ከሆነ፣ የማያቋርጥ የታችኛው ሆድ ወይም የዳሌ ሕመም ካለ፣ አሊያም ታምፖን ለመጠቀም የሚያስቸግር ከሆነ ሐኪም ማማከር ያስፈልጋል።
ምርመራው የሚከናወነው በውጫዊ የብልት አካል ምርመራ (Physical examination) ነው። ችግር የሚፈጥሩ ሽፋኖች ሲኖሩም «ሃይመኔክቶሚ» (Hymenectomy) የተባለ ቀላል የቀዶ ሕክምና ይደረጋል። በዚህ ሒደት ሐኪሙ ትርፍ የሆነውን ሽፋን በመክፈት ወይም በማስወገድ የወር አበባ ደም በነፃነት እንዲፈስና ሕመሙ እንዲቆም ያደርጋል።
በመጨረሻም ድንግልና ማለት በአንዲት ሴት የግል ውሳኔና ሕይወት የሚገለጽ ማኅበራዊ እና ግላዊ ጽንሰ-ሐሳብ እንጂ በአንድ ቀጭን ኅብረ-ሕዋስ የሚለካ አይደለም። ስለ ሰውነታችን ተፈጥሯዊ አወቃቀር ትክክለኛ ሳይንሳዊ ግንዛቤ መያዝ ሴቶችን ከአላስፈላጊ ፍርሃት፣ ጭንቀትና ማኅበራዊ መገለል ይታደጋል።




