የሆርሞን የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች እና የደም መርጋት
የሆርሞን የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች እርግዝናን ለመከላከል፣ የወር አበባ ዑደት መዛባትን ለማስተካከል እና አንዳንድ ከሆርሞን ጋር የተያያዙ የጤና ችግሮችን ለማከም በስፋት ጥቅም ላይ ይውላሉ። ምንም እንኳን ብዙ የተለመደ ባይሆንም አንዳንድ ኤስትሮጅን የያዙ የእርግዝና መከላከያዎች የደም የመርጋት አደጋን ሊጨምሩ ይችላሉ። ይህን ጽሁፍ በማንበብ ስለ አደጋው፣ ምልክቶቹ እና መከላከያ ዘዴዎቹ ማወቅ ሴቶች ስለ እርግዝና መከላከያ ምርጫቸው ትክክለኛ ውሳኔን እንዲያደርጉ ይረዳል።
1. የደም መርጋት ምንድን ነው?
የደም መርጋት ደም ከፈሳሽነት ወደ ጄል መሰል ወፍራም ንጥረ ነገር መለወጥ ሲሆን ደም መፍሰስን በተፈጥሮ ለማስቆም የሚረዳ መደበኛ የሰውነት ሂደት ነው። ነገር ግን በደም ሥሮች ውስጥ ደማችን ያለ አግባብ ሲረጋ፤ የደም ዝውውርን በመዝጋት ከባድ የጤና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። ከእርግዝና መከላከያ ሆርሞኖች ጋር የተያያዙ ሁለት ዋና ዋና የደም መርጋት ችግር አይነቶች አሉ ሲኖሩ፤ እነርሱም፦
- ጥልቅ የደም ሥር መርጋት (Deep Vein Thrombosis - DVT)፦ ብዙውን ጊዜ በእግር ወይም በጭን ውስጥ ባሉ ጥልቅ የደም ሥሮች ውስጥ የሚከሰት የደም መርጋት ነው።
- የሳንባ ደም ሥር መዘጋት (Pulmonary Embolism - PE)፦ ከረጋ ደም ላይ የተነሳ ክፍል በደም ዝውውር ወደ ሳንባ በመሄድ የሳንባን ደም ሥር ሲዘጋ የሚከሰት ለሕይወት አስጊ የሆነ ችግር ነው።
2. የሆርሞን የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች የደም መርጋት አደጋን እንዴት ይጨምራሉ?
አንዳንድ የሆርሞን የእርግዝና መከላከያዎች ኤስትሮጅን እና ፕሮጀስቲን የተባሉ ሁለት ሆርሞኖችን ይይዛሉ። እነዚህም ጥምር የሆርሞን የእርግዝና መከላከያዎች (Combined Hormonal Contraceptives) ይባላሉ። ለምሳሌ፦
- ጥምር የእርግዝና መከላከያ ኪኒኖች
- በቆዳ ላይ የሚለጠፉ የወሊድ መከላከያ ፓቾች
- በሴት ብልት ውስጥ የሚገቡ የወሊድ መከላከያ ቀለበቶች
ኤስትሮጅን ሆርሞን ጉበት የደም መርጋትን የሚያስተዳድሩ ፕሮቲኖችን እንዲያመነጭ በማድረግ በደም መርጋት ሂደት ላይ ተጽዕኖን ያሳድራል። ይህ ሁኔታ በተለይም ሌሎች የደም መርጋት አደጋ ምክንያቶች ባሉባቸው ሴቶች ላይ ደም በቀላሉ እንዲረጋ ሊያደርጋቸው ይችላል። ሆኖም እነዚህን የወሊድ መከላከያዎች የሚጠቀሙ ሁሉም ሴቶች የደም መርጋት ይገጥማቸዋል ማለት አይደለም።
3. የትኞቹ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች ከፍተኛ አደጋ አላቸው?
ሀ. ጥምር የሆርሞን የእርግዝና መከላከያዎች
እነዚህ ኤስትሮጅንን እና ፕሮጀስቲንን የያዙ ሲሆን፤ የደም መርጋት አደጋን ሊጨምሩ ይችላሉ። እንደ ኤን.ኤች.ኤስ መረጃ ከሆነ እነዚህን የእርግዝና መከላከያዎች ከሚጠቀሙ 1,000 ሴቶች ውስጥ አንዷ የደም መርጋት ሊያጋጥማት ይችላል።
ለ. ፕሮጀስቲንን ብቻ የያዙ የእርግዝና መከላከያዎች
እነዚህ የእርግዝና መከላከያዎች ኤስትሮጅን ሳይኖራቸው ፕሮጀስቲንን ብቻ የያዙ ናቸው። አብዛኞቹ ፕሮጀስቲንን ብቻ የያዙ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች የደም መርጋት አደጋን በከፍተኛ ሁኔታ አይጨምሩም። ሆኖም በመርፌ የሚሰጠው የእርግዝና መከላከያ በመጠነኛ ሁኔታ ከደም መርጋት አደጋ መጨመር ጋር ሊያያዝ ይችላል።
4. የደም መርጋት አደጋ የሚጨምርባቸው ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
አንዳንድ የጤና ችግሮችና የአኗኗር ሁኔታዎች የደም መርጋት አደጋን ይጨምራሉ። እነዚህም፦
- የቀድሞ የደም መርጋት ታሪክ፦ ቀደም ሲል በጥልቅ የደም ሥሮች ውስጥ የደም መርጋት ወይም የሳንባ ደም ሥር መዘጋት ችግር የተጠቁ ሴቶች።
- የቤተሰብ ታሪክ፦ በተለይም በወጣትነት ዕድሜ የደም መርጋት የነበረባቸው የቅርብ ቤተሰብ አባላት መኖር።
- ሲጋራ ማጨስ፦ በተለይም ከ35 ዓመት በላይ በሆኑና ኤስትሮጅንን የያዘ የእርግዝና መከላከያን በሚጠቀሙ ሴቶች።
- ውፍረት፦ ከመጠን በላይ የሆነ የሰውነት ክብደት መኖር።
- ለረጅም ጊዜ እንቅስቃሴ አለማድረግ፦ ለረጅም ጊዜ የአልጋ ቁራኛ ሆኖ መቆየት፣ ረጅም ጉዞ ላይ ሳይንቀሳቀሱ መቀመጥ ወይም ከበድ ካለ ቀዶ ጥገና በሚኖር የማገገም ጊዜ።
- በዘር የሚተላለፉ የደም መርጋት ችግሮች፦ ለምሳሌ የፋክተር ቪ ለይደን ሙቴሽን መኖር።
- እርግዝና እና ከወሊድ በኋላ ያለው ጊዜ፦ በእርግዝና ወቅትና ከወሊድ በኋላ የሰውነት ደም የመርጋት ዝንባሌ ሊጨምር ይችላል።
ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ አንዱ ወይም ከዚያ በላይ ያሉባቸው ሴቶች የወሊድ መከላከያ ከመጀመራቸው በፊት የጤና ባለሙያን ማማከር አለባቸው።
5. የእርግዝና መከላከያ በሚወስዱ ሴቶች ላይ የደም መርጋት አደጋ መቼ ይጨምራል?
ጥምር የሆርሞን የእርግዝና መከላከያን መጠቀም በጀመሩበት የመጀመሪያው ዓመት የደም መርጋት አደጋ መኖር አለሞኖር ልዩ ትኩረትን ይፈልጋል። ለብዙ ሳምንታት ወይም ከዚያ በላይ ለሚሆን ጊዜ መከላከያውን ካቋረጡ በኋላ እንደገና መጀመርም አደጋውን ሊጨምር ይችላል።
6. የደም መርጋት ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የደም መርጋት ምልክቶችን በጊዜ ማወቅ ከባድ ችግሮችን ለመከላከል ወሳኝ ነው።
ሀ. የጥልቅ የደም ሥር መርጋት (DVT) ምልክቶች
- በአንድ እግር ላይ እብጠት መከሰት።
- እግር በተለይም ባት አካባቢ ህመም ወይም ሲነካ ማመም።
- በእብጠቱ አካባቢ ሙቀት መጨመር።
- የቆዳ መቅላት ወይም ቀለም መቀየር።
ለ. የሳንባ ደም ሥር መዘጋት (PE) ምልክቶች
የደም መርጋት ወደ ሳንባ ሲሄድ የሚከተሉት ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ፦
- ድንገተኛ የመተንፈስ ችግር።
- በተለይም በጥልቀት ትንፋሽ ሲወሰድ የሚኖር የደረት ህመም።
- የልብ ምት መፍጠን።
- ደም የቀላቀለ አክታን ማሳል።
- ማዞር ወይም እራስን መሳት።
የሳንባ ደም ሥር መዘጋት ህይወት አስጊ የህክምና ሁኔታ ስለሆነ ከላይ የተዘረዘሩት ምልክቶች ካጋጠመዎት ወዲያውኑ የአስቸኳይ ህክምናን ያግኙ።
7. የደም መርጋት አደጋን እንዴት መቀነስ ይቻላል?
ምንም እንኳን የደም መርጋትን ሁልጊዜ መከላከል ባይቻልም፤ የሚከተሉት ልምዶች አደጋውን ለመቀነስ ይረዳሉ፦
- የእርግዝና መከላከያ ከመጀመርዎ በፊት የጤና ባለሙያ ያማክሩ።
- በተለይም ኤስትሮጅንን የያዙ መከላከያዎችን ሲጠቀሙ ሲጋራ ከማጨስ ይቆጠቡ።
- ጤናማ የሰውነት ክብደትን ይጠብቁ።
- በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ።
- ለረጅም ጊዜ ሳይንቀሳቀሱ ከመቆየት ይቆጠቡ።
- በአውሮፕላን፣ ባቡር ወይም አውቶቢስ ረጅም ጉዞን በሚያደርጉበት ጊዜ እግርዎን በተደጋጋሚ ያንቀሳቅሱ።
- ቀዶ ጥገና ከማድረግዎ በፊት የሚጠቀሙትን የወሊድ መከላከያ ለሐኪምዎ ያሳውቁ።
- የደም መርጋት ምልክቶችን ይወቁ፤ ምልክቶቹ ሲያጋጥሙዎትም በፍጥነት የህክምና እርዳታን ይፈልጉ።
8. የሆርሞን የእርግዝና መከላከያን ማቆም ይኖርብዎታል?
የደም መርጋት አደጋ አለ በሚል ምክንያት ሁሉም ሴቶች የሆርሞን የእርግዝና መከላከያን ማቆም አያስፈልጋቸውም። ለአብዛኞቹ ጤናማ ሴቶች የእነዚህ ዘዴዎች ጥቅም ከሚኖራቸው አደጋ የበለጠ ነው።
ሆኖም ቀደም ሲል የደም መርጋት ችግር ያጋጠማቸው፣ በዘር የሚተላለፍ የደም መርጋት ችግር ያለባቸው ወይም ሌሎች ከፍተኛ የአደጋ ምክንያቶች ያሉባቸው ሴቶች ሌላ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ መጠቀም ሊያስፈልጋቸው ይችላል።
በጤና ታሪክዎ መሠረት ደህንነቱ የተጠበቀ የእርግዝና መከላከያ ዘዴን ለመምረጥ የጤና ባለሙያን ያማክሩ። የደም መርጋት ምልክቶች ካጋጠሙዎት ግን ወዲያውኑ አስቸኳይ ህክምናን ያግኙ።
የሆርሞን የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች እርግዝናን ለመከላከል ውጤታማ ቢሆኑም፣ አንዳንዶቹ በተለይም ኤስትሮጅንን የያዙት የደም መርጋት አደጋን ሊጨምሩ ይችላሉ።
ግላዊ የአደጋ ምክንያቶችዎን ማወቅ፤ ተስማሚ የወሊድ መከላከያ መምረጥ እና የደም መርጋት ምልክቶችን በጊዜ መለየት ጤናዎን ለመጠበቅ ይረዳል።
ያስታውሱ! ምርጡ የወሊድ መከላከያ ዘዴ እርግዝናን በተሳካ ሁኔታ ከመከላከሉም በላይ ለግል የጤና ሁኔታዎ ተስማሚና ደህንነቱ የተጠበቀ የሆነው ነው።




