ልጅሽን ከማጥባትሽ በፊት ጡትሽን ማጠብ አለብሽ?

Elsabet Azezew
Nov 11, 2026
Gemini Generated Image o8bahso8bahso8ba

                                   ልጅሽን ከማጥባትሽ በፊት ጡትሽን ማጠብ አለብሽ?

አዲስ ለወለዱ እና ጡት ለሚያጠቡ እናቶች በብዛት ከሚነገሩ የተሳሳቱ አመለካከቶች አንዱ "ልጅሽን ከማጥባትሽ በፊት የጡትሽን ጫፍ በውኃና በሳሙና ማጠብ አለብሽ" የሚለው ነው። ነገር ግን የሕክምና ሳይንሱ የሚያረጋግጠው ተፈጥሮ ለዚህ በቂ ዝግጅት እንዳደረገች ነው።

በጡት ጫፍ ዙሪያ ባለው ጥቁር ክፍል (Areola) ላይ የሚገኙት ጥቃቅን የሞንትጎመሪ እጢዎች (Montgomery glands) የቆዳውን እርጥበት የሚጠብቅ ተፈጥሯዊ ቅባት ያመነጫሉ። ይህም ቅባት የቆዳውን ተፈጥሯዊ የአሲድ መጠን (pH) በመጠበቅ ጎጂ የሆኑ ባክቴሪያዎች እና ፈንገሶች (Yeast) እንዳያድጉ ይከላከላል።

ከማጥባትሽ በፊት ጡትሽን እንዳታጥቢ የሚመከርበት ሌላው አስደናቂ ምክንያት ደግሞ በእነዚህ እጢዎች የሚመረተው ተፈጥሯዊ ቅባት በእርግዝና ጊዜ ማኅፀን ውስጥ ከሚኖረው የእንሽርት ውሃ (Amniotic fluid) ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሽታ ያለው መሆኑ ነው። ሕፃናት ሲወለዱ የማየት አቅማቸው ውስን በመሆኑ ጡትን ለማግኘት የሚጠቀሙት የማሽተት ስሜታቸውን ነው። ስለዚህ ልጅሽ በሆድ ውስጥ እያለ የለመደው ይህ የታወቀ ሽታ ምቾት እንዲሰማው፣ እንዲረጋጋ እና ጡትን በትክክለኛው መንገድ ፈልጎ እንዲይዝ (Latching) ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል።

ስለሆነም ከማጥባትሽ በፊት ጡትሽን በተደጋጋሚ መታጠብ በተለይም ሳሙና መጠቀም በፍጹም አይመከርም። ሳሙና ይህን ተፈጥሯዊ ቅባት ስለሚያስወግደው የጡትሽ ጫፍ እንዲደርቅ፣ እንዲቆጣ፣ እንዲቆስል ወይም እንዲሰነጠቅ ያደርጋል።

                     ጡትሽን በተደጋጋሚ ማጠብ የሚያስከትላቸው ሌሎች ጉዳቶች

  • ለሕፃኑ ጠቃሚ የሆኑ ጥቃቅን ተህዋሲያንን (Microbiome) ያጠፋል

የጡት ጫፍ ላይ የሚገኙ ተፈጥሯዊ እና ጠቃሚ ባክቴሪያዎች ሕፃኑ በሚጠባበት ጊዜ ወደ ሆዱ በመግባት የምግብ መፈጨት ሥርዓቱ እና የበሽታ መከላከያ አቅሙ እንዲጠናከር ይረዳሉ። ጡትን በሳሙና ማጠብ እነዚህን ጠቃሚ ተህዋሲያንን ያጠፋል።

  • የሕፃኑን የምግብ ፍላጎት ሊቀይር ይችላል

የሳሙና፣ የሎሽን ወይም የሽቶ ቅሪት በጡት ጫፍ ላይ ከቀረ የጡት ወተቱን ተፈጥሯዊ ጣዕም እና ሽታ ስለሚቀይረው ሕፃኑ ጡት ላለመጥባት ሊያመነታ ወይም እምቢ ሊል ይችላል።

                          ታዲያ ምን ማድረግ አለብሽ? 

የጡት ንፅህና እና ክብካቤ መመሪያዎች ፦ 

  •  መደበኛ ገላ መታጠብ በቂ ነው 

ገላሽን በምትታጠቢበት ወቅት ጡትሽን በንጹሕ ለብ ያለ ውኃ ብቻ ማጠብ በቂ ነው። በጡትሽ ጫፍ ወይም በዙሪያው ባለው ጥቁር ክፍል ላይ ሳሙና ወይም አልኮል ያላቸውን የጽዳት ምርቶች አትጠቀሚ።

  •  ትኩረት ለእጅ ንጽህና

የጡት ማጥባት ዋናው ንጽህና የሚጀምረው ከእጅሽ ነው። ጡት ማጥባት ከመጀመርሽ በፊት ሁልጊዜ እጅሽን በሳሙና እና በውኃ በደንብ ታጠቢ።

  •  ላብ ወይም የደረቀ ወተት ሲኖር

ላብ ወይም ፈስሶ የደረቀ የጡት ወተት ካለ ከማጥባትሽ በፊት ለብ ባለ ውሃ ውስጥ በተነከረ ንጹሕ ጨርቅ ቀስ አድርገሽ ማበስ ትችያለሽ፤ በኃይል ማሸት አይመከርም።

  • ተፈጥሯዊውን የጡት ወተትሽን እንደ መድኃኒት ተጠቀሚበት 

ልጅሽን አጥብተሽ ስትጨርሺ ከጡትሽ ጥቂት ጠብታ ወተት በማውጣት የጡትሽ ጫፍ ላይ ቀስ አድርገሽ ቀቢው። የጡት ወተት ፀረ-ባክቴሪያ (Antibacterial) ይዘት ስላለው የጡት ጫፍ እንዳይሰነጠቅና እንዳይቆስል ይከላከላል።

  •  በአየር ማድረቅ

አጥብተሽ እንደጨረስሽ የጡት ማስያዣ (Bra) ከማድረግሽ በፊት የጡትሽ ጫፍ ለጥቂት ደቂቃዎች በአየር እንዲደርቅ ተይው።

  • ምቹ የጡት ማስያዣ ምረጪ

አየር የሚያስገቡ፣ ከጥጥ የተሰሩ እና በጣም ጥብቅ ያልሆኑ የጡት ማስያዣዎችን ተጠቀሚ። እንዲሁም የሚፈስ ወተት ለመምጠጥ የምትጠቀሚውን ፓድ (Breast pad) እርጥበት ሲይዝ ቶሎ ቶሎ መቀየርሽን አትርሺ።

በአጠቃላይ 

ጡት ማጥባት ተፈጥሯዊ ሂደት እንደመሆኑ መጠን ተፈጥሮ የራሷ የሆነ ራስን የመጠበቂያ እና የማጽጃ መንገድ አላት። ዋናው ትኩረት መሆን ያለበት የእጅ ንጽህናን መጠበቅ እና የጡት ጫፍ ሳይደርቅ ጤናማ ሆኖ እንዲቆይ ማድረግ ላይ ነው።

 

 

 

Comments (0)