የምግብ አለርጂ አንድ የተወሰነ ምግብ ከተበላ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የሚከሰት የሰውነታችን በሽታ የመከላከል ስርዓት ምላሽ ነው፡፡ይህን አለርጂ የሚያስከትል የምግብ ንጥረነገር በአነስተኛ መጠን ብንወስድ እንኳን የምግብ መፍጨት ስርዐታችን፣የአየር መተላለፊያዎቻችን ወይም ቆዳችን ላይ ምልክቶችን ልናይ እንችላለን። በአንዳንድ ሰዎች ላይ የምግብ አለርጂ ከባድ ምልክቶችን አልፎ “anaphylaxis” በመባል የሚታወቀው ለሕይወት አስጊ የሆነ ምላሽ ያስከትላል፡፡
የምግብ አሌርጂ ከ 6 እስከ 8 በመቶ የሚሆኑ ከ3 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናትን እና እስከ 3 በመቶ የሚሆኑትን አዋቂዎች ያጠቃል፡፡ ፈውስ ባይኖርም አብዛኞቹ ልጆች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ ሰውነታቸው ለምግብ አለርጂ የሚሰጠው ምላሽ እየተሻሻለ ይመጣል፡፡
አንዳንድ የምግብ አለርጂ ምልክቶች በስፋት ከተለመደው የምግብ አለመስማማት(food intolerance) ምልክቶች ጋር ሊምታቱ ቢችሉም የምግብ አለመስማማት የሰውነታችንን የበሽታ መከላከል ስርዐት የማያካትት ቀለል ያለ በሽታ ነው።
የምግብ አለርጂ ምልክቶች
ለአንዳንድ ሰዎች የምግብ አለርጂ ቀለል ያለ ምቾት መንሳት ሲሆን ለሌሎች ከባድ አልፎ ተርፎም ለሕይወት አስጊ ሊሆን ይችላል፡፡ የምግብ አለርጂ ምልክቶች አብዛኛውን ጊዜ ምግብ ከተመገቡ በኋላ ባሉት ጥቂት ደቂቃዎች እስከ ሁለት ሰዓታት ውስጥ ይታያሉ፡፡የተለመዱት የምግብ አለርጂ ምልክቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ:
- አፍ አካባቢ መደንዘዝ ወይም ማሳከክ
- የቆዳ ማበጥ፣ ማሳከክ ወይም ችፍ ማለት
- የከንፈር፣ የፊት፣ የምላስ እና የጉሮሮ ወይም የሌሎች የሰውነት ክፍሎች እብጠት
- የአፍንጫ መታፈን፣ ሲርሲር ማለት ወይም የመተንፈስ ችግር
- የሆድ ህመም፣ተቅማጥ፣ ማቅለሽለሽ ወይም ማስመለስ
የከባድ አለርጂ ምልክቶች
- የአየር መተላለፊያዎች ትቦዋች ማበጥ እና መጥበብ
- የደም ግፊት መቀነስ
- ፈጣን የልብ ምት
- ማዞር ፣ ራስ ምታት ወይም ራስን መሳት
መች ወደ ጤና ተቋም መሄድ አለብኝ?
ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶችን በተለይም የከባድ አለርጂ ምልክቶች ካስተዋሉ ወደ አቅራቢያዎ የሚገኝ የጤና ተቋም መሄድ ያስፈልግዎታል። ለዚህ በሽታ በአስቸኳይ ሕክምና ካልተደረገ እስከ ሞት ደረጃ የሚያደርስ የጤና እክል ነው።
የምግብ አለርጂ በምን ምክንያት ይከሰታል?
የምግብ አለርጂ የሚከሰተው የሰውነትዎ በሽታ የመከላከል ስርዓት አንድ የተወሰነ ምግብ ውስጥ ያለን ንጥረ ነገር በስህተት እንደ ጎጂ ለይቶ ይህን የሚያጠቃ ፀረ እንግዳ አካል (IgE) በሚያመርትበት ጊዜ ነው። በቀጣይ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ምግብ በሚመገቡበት ወቅት ይህ ፀረ እንግዳ አካል እንደ ሂስታሚን(histamine) ያሉ ንጥረነገሮች ወደ ደምስርዎ እንዲለቀቁ በማድረግ ከላይ የተጠቀሱትን የአለርጂ ምልክቶች ያስከትላሉ።
አብዛኛዎቹ የምግብ አለርጂዎች የሚከሰቱት በተወሰኑ ምግቦች ውስጥ ባሉ ፕሮቲኖች ነው። ከነዚህም መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ
- ለውዝ
- ዓሳ
- እንቁላል
- የላም ወተት
- ስንዴ
- አኩሪ አተር
ለምግብ አለርጂ አጋላጭ ምክንያቶች
- ዘር በቤተሰብ ተመሳሳይ በሽታ ወይም የአስም በሽታ ያለበት ሰው ካለ
- ሌሎች አለርጂዎች ለአንድ ምግብ አለርጂ ካለብዎ ለሌላውም አለርጂ የመኖር ዕድሉ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡
- ዕድሜ የምግብ አለርጂ ብዙውን ጊዜ በልጆች ላይ በተለይም አራሶች እና ታዳጊዎች ላይ በብዛት ይታያል፡፡
- አስም አስም እና የምግብ አለርጂ በተለምዶ አብረው ይከሰታሉ፡፡ ይህም በሚሆንበት ሰአት ሁለቱም የምግብ አለርጂ እና የአስም ምልክቶች የከፋ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡
ለከባድ የምግብ አለርጂ(anaphylaxis) የመጋለጥ እድልዎን ሊጨምሩ የሚችሉ ምክንያቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ:
- የአስም በሽታ መኖሩ
- በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ወይም ከዚያ በታች መሆን
- የምግብ አለርጂ ምልክቶችዎን ለመታከም መዘግየት
- የቆዳ ማበጥ፣ ማሳከክ ወይም ችፍታ አለመኖር
የምግብ አለርጂ የሚያስከትለው መዘዞች
- አናፊላክሲስ ወይም ከባድ ለሕይወት አስጊ የሆነ የአለርጂ ችግር
- የቆዳ አስም(atopic dermatitis)
የምግብ አለርጂ መከላከያ መንገዶች
- የለውዝ ምርቶችን ቀደም ብሎ ማስጀመር ልጆች ወደፊት ይህ ይዘት ያላቸውን የአለርጂ ተጋላጭነት ለመቀነስ እንደሚረዳ ይነገራል፡፡ ነገርግን የአለርጂ አምጪ ምግቦችን ለልጅዎ ከማስጀመርዎ በፊት ሐኪም ያማክሩ፡፡ ሆኖም የምግብ አለርጂ ቀድሞውኑ ከተከሰተ የአለርጂ ምላሽን ለመከላከል ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምልክቶችን የሚያስከትሉ ምግቦችን ማወቅ እና ማስወገድ ነው ፡፡
የምግብ አለርጂ እንዳለብዎ ካወቁ የሚከተሉትን እርምጃዎች ይከተሉ
- ምን እንደሚበሉ እና እንደሚጠጡ ይወቁ፡፡ የምግብ ይዘቶችን በጥንቃቄ ማንበብዎን እርግጠኛ ይሁኑ ፡፡
- ከባድ አለርጂ ካለብዎ ድንገት ምልክቶች ቢያጋጥምዎ መግባባት ላልችሉ ስለሚቀር የምግብ አለርጂ እንዳለብዎ ሌሎች እንዲያውቁ የሚያደርግ የሕክምና ማስጠንቀቂያ የእጅ ወይም የአንገት አምባር ያድርጉ፡፡ ለከባድ የአለርጂ ምላሽ ተጋላጭ ከሆኑ የኢፒነፍሪን (epinephrine) መድሃኒት ሁሌም አብሮት መሆን አለበት፡፡
- የውጪ ምግብ ቤቶች ውስጥ በሚያዙበት ሰዐት የምግቡን ይዘት ሙሉ በሙሉ በተጣራ ሁኔታ ይወቁ። አለርጂ ለመቀስቀስ አነስተኛ መጠን በቂ ስለሆነ የእርስዎ ምግብ የሚሰራበት እቃዎች ከአለርጂ ቀስቃሽ ምግቦች ጋር ንክኪ እንደሌለው ያረጋግጡ። በተቻለ መጠን በቤትዎ ውስጥ የተዘጋጀ ምግብ እንዲመገቡ ይመከራል።
- በሚጠራጠሩበት ጊዜ አለመመገብን ይምረጡ፡፡ በምግብ ቤቶች እና በድግሶች ላይ አለርጂ ቀስቃሽ ምግቦችን የመመገብ እድል ሰፊ ስለሆነ የምግቡን ይዘት በጥንቃቄ አጣርተው እርግጠኛ መሆን ካልቻሉ አነስተኛ መጠን ራሱ የአለርጂ ምልክቶችን ሊያስከትል ስለሚችል አለመመገብን እንዲመርጡ ይመከራል።
- ልጅዎ የምግብ አለርጂ ካለበት አብረውት ለሚወሉ አዋቂዎች በሙሉ ስለልጅዎ ሁኔታ እንዲያውቁ እና መውሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች እንዲገነዘቡ ማድረግ ተገቢ ነው። ለልጅዎም የበሽታውን ምልክቶች በአግባቡ እንዲለይ እና እርዳታ እንዲያገኝ ያስገንዝቡ።



