- ሲጋራ ማጨስ ለበርካታ አካላዊ እና ሥነ አእምሮአዊ በሽታዎች መከሠት መንሥኤ ነው። በዓለም የጤና ድርጅት ጥናት መሠረት በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ኢትዮጵያ 4 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ሲጋራ ያጨሳል።
- ሲጋራ በውስጡ ኒኮቲን የተባለ ንጥረ ነገር አለው። ኒኮቲን የአንጎልን ነርቭ አስተላላፊዎችን በማወክ ጊዜያዊ የሆነ የደስታ ስሜት እንዲፈጠር የሚያደርግ ንጥረ ነገር ነው።
- ሲጋራን የሚያጨሱ ሰዎች የለመዱትን የመነቃቃት እና ደስታ ስሜት ለማምጣት የሚወስዱትን የኒኮቲን መጠን በየጊዜው መጨመር ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ የተነሣ የሲጋራ ፍጆታቸውን ለመጨመር ይገደዳሉ።
- በተጨማሪም ማጨስን ለማቆም በሚሞክሩበት ጊዜ ደስ የማይል አካላዊ እና ስሜታዊ ለውጦች ይኖሯቸዋል።
ለሲጋራ ማጨስ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች እነማን ናቸው?
- ዕድሜ፤ አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች ወይም በዓሥራዎቹ ዕድሜ የአሉ ሰዎች በሲጋራ ሱስ የመያዝ ዕድላቸው ሰፊ ነው።
- የዘረ መል ተጽዕኖ፤ የዘረ መል አወቃቀር የአንጎል ሕዋሳት ለሲጋራ (Nicotine) ጥገኝነት እንዲዳረጉ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።
- የወላጅ ተጽዕኖ እና የአቻ ግፊት፤ የሚያጨሱ ወላጆች ወይም የሚያጨሱ አቻ ጓደኞች የአሏቸው ሰዎች የማጨስ ዕድላቸው ሰፊ ነው።
- የሥነ ልቦና ችግሮች፤ ለምሳሌ ድባቴ፣ ስኪዞፍሬኒያ ወይም ጭንቀት ሲጋራ የማጨስ ዕድልን ይጨምራሉ፡፡
- የአልኮሆል መጠጥ እና ሌሎች አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች ሲጋራ የማጨስ ዕድላቸው ሰፊ ነው።
ሲጋራ ማጨስ የሚያመጣቸው ሥነ ልቦናዊ ጉዳቶች ምንድናቸው?
- ሲጋራ ማጨስ ከሚያስከትላቸው ሥነ ልቦናዊ ቀውሶች ውስጥ ዋነኛው የሲጋራ -ጥገኝነትን (Nicotine dependence) ማስከተል ነው። የሲጋራ ጥገኝነት ምልክቶች በየትኛውም የሲጋራ መጠን ላይ ሊከሠቱ ይችላሉ።
የሲጋራ ጥገኝነት ምልክቶች ምንድናቸው?
- ሲጋራ ማጨስን ማቆም አለመቻል፤
- ይህ ምንም እንኳን ሲጋራ ማጨስ ለማቆም ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ግን አለመቻል ነው።
- ማጨስ ለማቆም ሲሞክሩ የተለያዩ አካላዊ እና ሥነ አእምሮአዊ ችግሮች መታየት፤
- ለምሳሌ፤ ለማጨስ ከፍተኛ ፍላጎት መኖር፣ ጭንቀት፣ ብስጭት፣ መረጋጋት አለመቻል፣ ትኩረትን የመሰብሰብ ችግር፣ የረኃብ ስሜት መጨመር፣ እንቅልፍ ማጣት፣ የሆድ ድርቀት ወይም ተቅማጥ መኖር ናቸው።
- አሳሳቢ የጤና (የሳንባ ወይም የልብ) ችግር እንደአለባቸው እያወቁ እንኳን ማጨስን መቀጠል፤
- የማኅበራዊ ሕይወት ተሳትፎን መቀነስ፡፡ ሲጋራ ማጨስ የሚከለከልባቸው ቦታዎች ወይም ዝግጅቶች ጋር ከመሔድ መቆጠብ፤
- ለምሳሌ፤ ከቤተሰብ ወይም ከጓደኞች ጋር መገናኘት፣ ምግብ ቤቶች ወይም መዝናኛ ቦታዎች መሔድ መቀነስ ናቸው።
ሲጋራ ማጨስ የሚያስከትለው አካላዊ የጤና ጉዳቶች ምንድናቸው?
- የሲጋራ ጭስ በውስጡ ከ 60 በላይ ካንሰርን የሚያስከትሉ ኬሚካሎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ጎጂ ንጥረ ነገሮች አሉት፡፡
- ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች በአንፃሩ ከማያጨሱ ሰዎች በተለየ መልኩ አማካይ የዕድሜ ጣሪያቸው ዝቅ ያለ ነው።
- የሳንባ ካንሰር ወይም ሥር የሰደደ የሳንባ በሽታ።
- ሲጋራ ለሳንባ ካንሰር መከሠት እና ሞት ዋነኛው መንሥኤ ነው። በተጨማሪም ሊሎች እንደ ኤምፊዚማ፣ ብሮንካይተስ፣ አስም እና የመሳሰሉ የሳንባ በሽታዎችን ያስከትላል። አስቀድሞ ከአሉም እንዲባባሱ ያደርጋል።
- ሌሎች ሲጋራ ማጨስ የሚያመጣቸው የካንሰር ዓይነቶች ምን ምን ናቸው?
- ሲጋራ ማጨስ የአፍ፣ የጉሮሮ፣ የፊኛ፣ የቆሽት፣ የኩላሊት፣ የማሕፀን ጫፍ፣ የደም ካንሰር እና ለሌሎች በርካታ የካንሰር ዓይነቶች ተጋላጭነትን ይጨምራል፡፡
- በአጠቃላይ ሲጋራ ማጨስ በካንሰር የመሞት ዕድልን 30 በመቶ ያህል ይጨምረዋል፡፡
- የልብ ድካም እና የደም ዝውውር ሥርዓት ሕመም
- በስትሮክ የመመታት እና የመሞት ዕድልን ይጨምራል።
- የስኳር በሽታ
- የዐይን ሕመም
- መካንነት እና ስንፈተ ወሲብ
- በእርግዝና ወቅት ችግር መፈጠር (ምጥ የአለ ጊዜው መጀመር፣ ከጤናማ ክብደት በታች የሆነ ልጅ መውለድ) እና
- የጥርስ እና የድድ ብግነት ወይም መቆጣት ናቸው።
ማጨስ ለማቆም ምን እናድርግ?
- በራስ ተነሣሽነት ያለጤና ባለሙያ ርዳታ ማጨስን ለማቆም የሚደረጉ ሙከራዎች ረዥም ጊዜ ከመውሰዱም በላይ ውጤታማ ላይሆን ይችላል።
- ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመመካከር፣ የተለያዩ መድኃኒቶች እና የሥነ ልቦና ምክክሮችን በማድረግ ከሲጋራ ጥገኝነት ነፃ መውጣት ይቻላል።
መድኃኒቶች
- የጤና ባለሙያዎች የማጨስ ፍላጎትን የሚቀንሱ እና ማጨስ የመተው ምልክቶችን የሚያስታግሡ መድኃኒቶች በመስጠት ሕክምናውን ያቀላጥፉታል።
የሥነ ልቦና ምክክር
- የሥነ ልቦና ምክክር ማድረግ ሲጋራን ለመተው የሚያስፈልጉ ክሂሎቶችን ለማዳበር ይጠቅማል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከጤና ባለሙያ ጋር ጊዜ ወስዶ ስለአኗኗር ዘይቤዎች እና ስለ ሥራ ዕቅድ ማውጣት እንዲሁም በትግበራው ላይ መመካከር ያስፈልጋል።
- ከቤተሰብ፣ ጓደኛ እና ተመሳሳይ ችግሮች ከአሉባቸው ሰዎች ጋር በመጣመር የልምድ ልውውጥ ማድረግ ጠቃሚ ነው።
ኤሌክትሮኒክ ሲጋራዎች (e-Cigarettes)
- ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ የኤሌክትሮኒክ ሲጋራዎችን ማጨስ ከሲጋራ ሱስ ለመላቀቅ መፍትሔ መሆን አይችልም፡፡ ሲጋራን ለመተካት ተብሎ ሌሎች ኒኮቲንን የያዙ ንጥረ ነገሮችን (ጭስ አልባ ትንባሆ፣ ሺሻ፣ ኤሌክትሮኒክ ሲጋራዎች) መጠቀም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል።
ሲጋራ ማጨስ ለማቆም አስበን የጤና ባለሙያ ጋር ለመሔድ ስንዘጋጅ ምን ማድረግ አለብን?
የጤና ባለሙያን ለማማከር ስናስብ የሚከተሉትን ማድረግ ለሕክምናው የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
- የማጨስ ፍላጎት የሚያነሣሣብዎትን ነገሮች ወይም ሁኔታዎች ማስተዋል፤ ወይም ሲያጨሱ የአለውን ሁኔታን በዝርዝር መጻፍ፡፡
- ከማጨስ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ምልክቶችን እና ለምን ያህል ጊዜ እንደሚያጨሱ ያስተውሉ።
- የሚወስዱትን መድኃኒቶች ማስታወስ
- በሕክምናው ወቅት የቤተሰብ አባል ወይም ጓደኛን መጋበዝ።




