የሴት ብልት ውስጠኛ ክፍልን በፈሳሽ ማጽዳት(Vaginal Douching) ጠቃሚ ነው ወይስ ጎጂ?

Elsabet Azezew
Sep 3, 2025
undefined

          የሴት ብልት ውስጠኛ ክፍልን በፈሳሽ ማጽዳት(Vaginal Douching) ጠቃሚ ነው ወይስ ጎጂ?

 

         በአሜሪካ እድሜያቸው ከ 15-44 ከሆኑ ሴቶች መካከል 20% የሚሆኑት የብልታቸውን የውጠኛው ክፍል ያፀዳሉ። ይህም ልማድ በአፍሪካ ሴቶች በላቀ ደረጃ የሚተገበር እንደሆነ ሲነገር  በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከ80-90% የሚሆኑ ሴቶች ይህን ልምምድ ይተገብራሉ።ይህንንም በውኃ የሚያደርጉ ሲሆን ውኃው ውስጥም እንደ ኮምጣጤ ወይም ቬኔጋር ፣ ቤኪንግ ሶዳ፣ አዮዲን፣ ፀረ-ተህዋስያን ወይም አንቲሰፕቲክ እና ሌሎች ሽታ ያላቸው ምርቶችን ይጠቀማሉ ። ይህንን ውህድ ወደ ብልት ውስጥ ለመርጨት ጠርሙስ ፣ የፕላስቲክ ከረጢት ወይም ጣቶቻቸውን ይጠቀማሉ ። 

 

        ብዙ ሴቶች ንጽህናን ለመጠበቅ ከማስቻል በተጨማሪ መጥፎ ጠረንን ለማስወገድ፣ ከወር አበባ በኋላ ደምን ለማጽዳት፣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል እና ከግንኙነት በኋላ እርግዝናን እንዳይፈጠር ለመከላከል በሚል የብልታቸውን የውጠኛውን ክፍል ያፀዳሉ። 

 

       ይሁን እንጂ የጤና ባለሙያዎች ከእነዚህ ዓላማዎች ለአንዱም ውጤታማ እንዳልሆነ ይናገራሉ። ከዚህም በላይ ለኢንፌክሽኖች፣ ለተለያዩ የእርግዝና ችግሮች እና ለሌሎች የጤና እክሎች የመጋለጥ እድልን ሊጨምር እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።

               ዶውሺንግ ጎጂ ወይስ ጠቃሚ ?

       የአሜሪካ የጽንስና ማህፀን ህክምና ኮሌጅ (American College of Obstetrics and Gynecology (ACOG)) ሴቶች የብልታቸውን የውስጠኛውን ክፍል እንዲያፀዱ አይመክርም።  የሴት ብልት በተፈጥሮ ጤናማ የፒኤች (pH) ሚዛን ያለው እና ኢንፌክሽን እና ብግንነትን ለመከላከል በሚረዱ ጤናማ ባክቴሪያዎች (vaginal flora) የተሞላ ነው።

       የብልትን የውስጥ ክፍል ማፅዳት ብልት ውስጥ ያሉትን ጤናማ ባክቴሪያዎች በማስወገድ ወይም በከፍተኛ ደረጃ ችግር አምጪ ባክቴሪያዎች እንዲራቡ ያግዛል። ይህም ለኢንፌክሽን፣ ለብግነት እና ለሌሎች የከፋ ችግሮች ያጋልጣል።  

በአጠቃላይ የብልትን የውስጠኛውን ክፍል ማፅዳት በጣም ጎጂ ልማድ ነው። ይህን ካደርጉ ከሚያጋጥሞት የጤና ችግሮች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ 

 

  • የእርግዝና ችግሮች

  በሳምንት ከአንድ ጊዜ በላይ የብልታቸውን የውስጠኛውን ክፍል የሚያፀዱ ሴቶች ይህን ልማድ ከማያደርጉ ሴቶች ይልቅ ለማርገዝ የበለጠ ይቸገራሉ። ከዚህ በተጨማሪ ከማህፀን ውጪ እርግዝና (ectopic pregnancy) የመፈጠር እድልን እስከ 76% ድረስ ሊጨምር ይችላል። አዘውትረው ዶች የሚያደርጉ ሴቶች መውለድ ካለባቸው ቀን ቀደም ብለው የመውለድ፣ የፅንስ መጨንገፍ እና ሌሎች የእርግዝና ችግሮች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው።

 

  • ኢንፌክሽን 

     ብልት ውስጥ ያለው ጤናማ የባክቴሪያ ሚዛን የብልት እርሾ (ይስት) እንዳይፈጠር ይከላከላል። ይህንን ተፈጥሯዊ ሚዛን የብልትን የውስጠኛውን ክፍል በማፅዳት ማጥፋት ፈንገስ እንዲራባ በማድረግ የእርሾ(የይስት) ኢንፌክሽን እንዲፈጠር ያደርጋል።

     በተመሳሳይ የብልትን የውስጠኛውን ክፍል የምታፀዳ ሴት ባክቴሪያል ቫጂኖሲስ (bacterial vaginosis) ለተባለ ኢንፌክሽን የመጋለጥ እድሏ ይህን ከማታደርግ ሴት ጋር ሲነፃፀር በ አምስት እጥፍ ከፍ ያለ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ዶውሺንግ ኢንፌክሽንን ሊያባብስ የሚችል ሲሆን አንዲት የብልት ኢንፌክሽን ያለባት ሴት የብልትዋን የውስጠኛ ክፍል የምታፀዳ ከሆነ ኢንፌክሽኑ ወደ ሌሎች የመራቢያ አካል ክፍሎች የመሰራጨት እድሉ ከፍተኛ ነው።

 

  • ፔልቪክ ኢንፍላማቶርይ ዲዝዝ (Pelvic Inflammatory Disease (PID)) 

    ፔልቪክ ኢንፍላማቶርይ ዲዝዝ የማህፀን፣ የማህፀን ትቦ እና የእንቁልጢ ኢንፌክሽን ሲሆን የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የብልታቸውን የውስጠኛው ክፍል የሚያፀዱ ሴቶች ለዚህ ኢንፌክሽን የመጋለጥ እድላቸው በ73% ከፍ ያለ እንደሆን ያመለክታሉ።

 

  • የማህፀን በር ካንሰር

     በሳምንት ቢያንስ አንድ ጊዜ ዶውሺንግ ማድረግ የማህፀን በር ካንሰር የመከሰት እድልን እንደሚጨምር ይነገራል። 

Comments (0)