የሴት ብልትን በእንፋሎት ማጠን (Vaginal Steaming) አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ያውቃሉ ?

Elsabet Azezew
Sep 3, 2025
undefined

        የሴት ብልትን በእንፋሎት ማጠን (Vaginal Steaming) አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ያውቃሉ ?

        የሴት ብልትን በእንፋሎት ማጠን ብልትን እና ማህጸንን ለማፅዳት እንዲሁም ከወር አበባ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ህመምን እና የሆድ መነፋትን ለመቀነስ በሚል የሚደረግ ከጥንት ጀምሮ የመጣ ልማድ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ልማድ ሙቀትን ከመስጠት ውጪ የጤና ጥቅም አለው? ደህንነቱስ የተጠበቀ ነው? በዚህ ፅሁፍ ስለ ብልትን በእንፋሎት ማጠን (vaginal steaming) እንዳሳለን ።

 

                   የሴት ብልትን በእንፋሎት ማጠን (vaginal steaming) ምንድን ነው?

          የሴት ብልትን በእንፋሎት ማጠን (vaginal steaming) የተለያዩ ባህላዊ ዕፅዋቶችን በመጠቀም የተቀመመ እና ሙቅ በሆነ የእንፋሎት ውሃ የመታጠን ሂደት ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እ.ኤ.አ. በ 2012 በኢንዶኔዥያ ፣ በሞዛምቢክ ፣ በደቡብ አፍሪካ እና በታይላንድ ባደረጋቸው ጥናቶች ብዙ የሃገራቸው ሴቶች የብልት ጤናን ለመጠበቅ በሚል በእንፋሎት ወይም በጭስ ብልታቸውን ያጥናሉ። ይህን ልማድ አንዳንድ ሴቶች ከወሊድ በኋላ ለአጭር ጊዜ ብቻ ሲያደርጉ ሌሎች ደግሞ ብልት ለማጥበብ (Vaginal tightening) እና በአጠቃላይ ውበትን ለመጠበቅ በሚል ያፈጽማሉ።

 

የሴት ብልትን በእንፋሎት ማጠን (vaginal steaming) አለው ከሚባሉት ጥቅሞች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ 

  • በሰውነት ውስጥ የተመጣጠነ ሆርሞን እንዲኖር ያደርጋል
  • ማህጸንን ማጽዳት
  • ከወሊድ በኋላ በፍጥነን ለማገገም ያግዛል 
  •  ህመምን ያስታግሳል
  • ራስ ምታትን ያስታግሳል
  •  ጭንቀትን እና ድካምን ያስወግዳል 

            ነገር ግን የሴት ብልትን በእንፋሎት ወይም በጭስ ማጠን እነዚህን ጥቅሞች እንደሚሰጥ የሚጠቁም ምንም አይነት ሳይንሳዊ ማስረጃ የለም። ከዚህም በተጨማሪ እንፋሎቱ ወደ ብልት ውጫዊ ክፍል እንጂ ወደ ማህጸን ጫፍም ሆነ ወደ ማህጸን የመድረስ አቅም የለውም። 

 

                   የሴት ብልትን በእንፋሎት ወይም በጭስ ማጠን ደህንነቱስ የተጠበቀ ነው ?

         ሐኪሞች የሴት ብልትን በእንፋሎት ማጠን አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። ይህም የሆነበት ምክንያት የሴት ብልት ቆዳ በጣም ስስ ስለሆነ በቀላሉ ሊጎዳ ወይም በእንፋሎቱ ሊቃጠል ስለሚችል ነው። ከዚህ በተጨማሪም ብልትን ለእንፋሎት እና መዓዛ ላላቸው የዕፅዋት ውህዶች ማጋለጥ የብልት የአሲድ ፒኤችን እንዲለወጥ ስለሚያደርግ የባክቴሪያ ሚዛንን ያዛባል ፤ ይህም ባክቴሪያል ቫጂኖሲስ(bacterial vaginosis) ለተባለው የብልት ኢንፌክሽን እና ለይስት/ ፈንገስ ኢንፌክሽን ያጋልጣል። ብልትን ለማጠን ጥቅም ላይ የሚውሉ መቀመጫዎች እና የተለያዩ እቃዎች በደንብ የፀዱ ካልሆኑም ኢንፌክሽንን ሊያስከትሉ እንደሚችሉም ሐኪሞች ይጠቁማሉ። 

 

  •  አንዲት ሴት ነፍሰ ጡር ከሆነች ይህን ልምምድ በፍጹም ማድረግ የለባትም ምክያቱም በእርግዝና ወቅት ለከመጠን በላይ ሙቀት መጋለጥ የተለያዩ ውስብስብ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ሊያስከትል ስለሚችል ነው።  

     በአጠቃላይ የሴት ብልት እራስን የሚያጸዳ አካል በመሆኑ በእንፋሎትም ሆነ በሌሎች መንገዶች ለማጽዳት መሞከር አስፈላጊ አይደለም። 

Comments (0)