ሁሉም ሰው የተለመዱ የእርግዝና ምልክቶችን ያውቃል፦ የወር አበባ መቅረት፣ የጡት ማበጥ፣ ማቅለሽለሽ እና ሁልጊዜ ድካም መሰማት። ነገር ግን ነፍሰ ጡር ሰዎች ከእነዚህ የመጀመሪያ ምልክቶች በተጨማሪ ብዙ ተጨማሪ ስሜቶች ያጋጥማቸዋል።
በእርግዝና ጊዜ የሚኖር የሆርሞኖች መለዋወጥ፣ ድንገተኛ፣ እንግዳ ወይም እንዲያውም ከባድ የሚመስሉ ምልክቶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ከእነዚህ ምልክቶች መካከል አንዳንዶቹ ገና በእርግዝና የመጀመሪያ ሳምንታት ውስጥ ሊታዩ ይችላሉ።
ሊያዩዋቸው የሚችሏቸው ጥቂት ያልተለመዱ የእርግዝና ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፤
1. የብረት ጣዕም መኖር
በእርግዝና ወቅት የኢስትሮጅን (Estrogen) እና የፕሮጀስትሮን (Progesterone) ሆርሞኖች መጨመር በብዙ ነፍሰ ጡር ሰዎች ላይ የጣዕም ለውጥ ሊያስከትል ይችላል።
አንዳንድ ነፍሰ ጡሮች ጣዕምን የሚያዛባ ስሜት ሊያዳብሩ ይችላሉ። ይህ ምግቦች የብረት ጣዕም፣ መራራ ወይም አነስተኛ ጣፋጭነት እኒዶራቸው ያደርጋል።
ይህንን ለማከም የሚረዳ ፍቱን መድኃኒት ባይኖርም፣ የጣዕም ለውጡን ለመቀነስ የሚከተሉትን መንገዶች መሞከር ይችላሉ፦
- ስኳር የሌለው ማስቲካ ማኘክ።
- በምግብዎ ላይ ተጨማሪ ቅመማ ቅመሞችን መጨመር።
- የብረቱን ጣዕም ለመቀነስ ጣፋጭነት ወይም ቆምጣጣነትያላቸውን ምግቦች መጨመር (ለምሳሌ እንደ ሎሚ)።
2. የማዞር ስሜት
በእርግዝና የመጀመሪያ ሶስት ወራት ውስጥ ነፍሰ ጡር ሰዎች የመላወስ ወይም የማዞር ስሜት መሰማት ያልተለመደ ነገር አይደለም። መንስኤውም እርግዝና የደም ግፊት እንዲቀንስ እና የደም ስሮች እንዲለጠጡ ያደርጋል። የደም ስር መለጠጥ አቋምዎን በፍጥነት ሲቀይሩ (ለምሳሌ ከተኙበት ወይም ከተቀመጡበት በድንገት ሲነሱ) የማዞር እንዲሰማዎት ሊያደርግ ይችላል። በተጨማሪም በድካም፣ ዝቅተኛ የደም ስኳር መጠን እና ውጥረት ምክንያትም ሊከሰት ይችላል።
ለመቀነስ የሚረዱ ምክሮች
- አቋምዎን ሲቀይሩ (ሲቆሙ ወይም ሲቀመጡ) በጥንቃቄ እና በዝግታ ያድርጉ።
- በቂ ውሃ ይጠጡ
- የማዞር ስሜት ሲሰማዎ ወዲያውኑ ይቀመጡ ወይም ይተኙ።
- ትንሽ ትንሽ ቶሎ ቶሎ ይብሉ
- ይህ ስሜት በጣም ከባድ ከሆነ ወይም አብሮት ሌሎች አሳሳቢ ምልክቶች ካሉ ሐኪም ማማከር ያስፈልጋል።
3. የአፍንጫ ደም መፍሰስ
በእርግዝና ወቅት የሆርሞን ለውጦች በመኖራቸው ምክንያት መንሰር የተለመደ ነው። ሰዎች በነቁበትም ሆነ በእንቅልፍ ላይ እያሉ ሊነስራቸው ይችላል፣ እና ደሙ ከአፍንጫቸው ከመውጣቱ በፊት በጉሮሮአቸው ውስጥ ሊሰማቸው ይችላል።
ነስሩ አደገኛ የሚሆነው አልፎ አልፎ ሲሆን በአብዛኛው በቤት ውስጥ ሊቆጣጠሩት የሚችሉት ነው። ደሙ በ15 ደቂቃ ውስጥ ካልቆመ ወይም መጠኑ ቢዙ ከሆነ ሐኪም ማነጋገር ያስፈልጋል።
4. የሆድ ድርቀት
በእርግዝና ወቅት የሆድ ድርቀት የተለመደ ስሜት ነው። ምክኛቶቹም
- የሆርሞን ለውጥ:
- የማህፀን እድገት: በእርግዝና ወቅት ማህፀንዎ ሲያድግ አንጀትዎ ቦታ ሊቀይር ይችላል፣ ይህ ደግሞ መደበኛ ሰገራ መውጣትን ሊያስተጓጉል ይችላል።
- የብረት ንጥረ ነገር (Iron): የሚወስዷቸው የቅድመ ወሊድ አይረን የሆድ ድርቀትን ሊያስከትል ይችላል።
- የምግብ መፈጨት መቀነስ: ጥረ ነገሮች ወደ ደምዎ ውስጥ ገብተው ልጅዎ ጋር ለመድረስ በቂ ጊዜ እንዲያገኝ ሲባል በእርግዝና ወቅት የምግብ መፈጨት ስርዓትዎ ይቀዘቅዛል።
የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ ሊረዳዎ ይችላል፦
- ብዙ ፋይበር ያላቸውን ምግቦች መመገብ።
- ብዙ ፈሳሽ መጠጣት።
- መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ።
- አስፈላጊ ከሆነ፣ ከሐኪምዎ ጋር በመነጋገር ለእርግዝናዎ ደህንነቱ የተጠበቀ ሰገራ ማለስለሻ መጠቀም ይችላሉ።
5. የጠነከረ የማሽተት ስሜት
በእርግዝና መጀመሪያ ላይ የኢስትሮጅን ሆርሞን መጠን መጨመር የማሽተት ስሜትዎን ሊያጠናክረው ይችላል፤ ይህም ቀደም ሲል ምንም የማይመስሉ ሽታዎች ከመጠን በላይ ጠንካራ ሆነው እንዲሸቱ ያደርጋል። ማቅለሽለሽ እንዲሰማዎም ሊያደርግ ይችላል።
6. ያበጠ ወይም የቀላ አፍንጫ እና የአፍንጫ መደፈን
የደም ፍሰት መጨመር በአፍንጫ ውስጥ እብጠትን ወይም የደም ስሮች መስፋፋትን ሊያስከትል ይችላል የሚሉ ግምቶች አሉ። ይህ ምልክት በእርግዝና ወቅት በሆርሞን ምክንያት ከሚመጣ የአፍንጫ መታፈን ጋር ተያይዞ ሊታይ ይችላል።
የአፍንጫ መዘጋትን ለማከም የሚከተሉትን መጠቀም ሊረዳ ይችላል፦
- የአየር እርጥበትን የሚጨምር መሳሪያ መጠቀም።
- በጨው መታጠብ፦ የአፍንጫ ውስጥ ጨው በውሃ አድርጎ መታጠብ
7. የደም ነጠብጣብ ወይም "ሐሰተኛ" የወር አበባ
በእርግዝና መጀመሪያ ላይ አራት ነፍሰ ጡር ሴቶች መካከል በአንዷ ላይ የደም ነጠብጣብ ወይም ቀላል ደም መፍሰስ ይከሰታል።ይህ እንቁላሉ የማህፀን ግድግዳ ላይ ለመጣበቅ ሲሞክር ቀላል ደም መፍሰስ ሊከሰት ይችላል። ይህ ክስተት ከተፀነሰ ከሁለት ሳምንት በኋላ አካባቢ ሊፈጠር ይችላል።
የደም መፍሰሱ በሌሎች ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል፤ ከእነዚህም መካከል፦
- የማህፀን በር መበሳጨት (Cervical Irritation)
- ከማህፀን ውጭ እርግዝና (Ectopic Pregnancy)
- የፅንስ መውረድ (Threatened Miscarriage)
ቀላል ደም መፍሰስዎ እየከበደ ከሄደ ወይም ከባድ ቁርጠት፣ የጀርባ ህመም ወይም ድንገተኛና ከባድ ህመም አብሮት ከመጣ፣ ወዲያውኑ የህክምና እርዳታ ማግኘትዎን ያረጋግጡ።
8. ከማህጸን ፈሳሽ መውጣት
አብዛኛዎቹ ነፍሰ ጡር ሰዎች በእርግዝና የመጀመሪያ ሶስት ወራት ውስጥ እና በእርግዝናው ጊዜ ሁሉ የፈሳሽ መጨመር ያጋጥማቸዋል። ይህ ፈሳሽ በተለምዶ የሚጣበቅ፣ ነጭ ወይም ፈዛዛ ቢጫ ቀለም ያለው ይሆናል።
በእርግዝና ወቅት የሆርሞን መጠን መጨመር እና የደም ዝውውር መብዛት የፈሳሹን መጠን ይጨምራል። ይህ ፈሳሽ የማኅጸን ጫፍዎ እና የብልት ግድግዳዎችዎ በሚለሰልሱበት ጊዜ ኢንፌክሽኖችን ለመከላከል ሊረዳ ይችላል።
የሚወጣው ፈሳሽ የሚከተሉትን ምልክቶች ማሳየት ከጀመረ ሐኪም ማነጋገር ያስፈልግዎታል፦
- መጥፎ ሽታ ካለው
- የማቃጠል ስሜት ካለው
- የሚያሳክክ ከሆነ
- አረንጓዴ-ቢጫ ቀለም ከተለወጠ
- በጣም ወፍራም ወይም ውሃማ ከሆነ
እነዚህ ምልክቶች የኢንፌክሽን ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ።
9. የስሜት መለዋወጥ እና የወሲብ ፍላጎት ለውጦች
የሚለዋወጡት ሆርሞኖችዎ በስሜትዎ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። ባልተለመደ ሁኔታ ማልቀስ ወይም ስሜታዊ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ የስሜት ለውጦች በእርግዝና መጀመሪያ ላይ የተለመዱ ናቸው።
የሆርሞን ለውጡ የግብረ ሥጋ ፍላጎትዎ እንዲለዋወጥ ሊያደርግ ይችላል፤ ሊቀንስ ወይም ሊጨምር ይችላል።
10. ማቃር
በእርግዝና ወቅት የሚለዋወጡት ሆርሞኖች በሆድዎ እና በጉሮሮዎ መካከል ባለው ቫልቭ (valve) ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ይህ አካባቢ በእርግዝና ወቅት ዘና ስለሚል፣ የሆድ አሲድ ወደ ጉሮሮዎ እንዲመለስ ያስችላል፤ ይህም ማቃር ያስከትላል።
አነስተኛና በተደጋጋሚ መመገብ እና አንዳንድ ምግቦችን ማስወገድ ሊረዳ ይችላል። እነዚህ ሊያስወግዷቸው የሚገቡ ምግቦች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
- የተጠበሱ ምግቦች
- ቅመም የበዛባቸው ምግቦች
- ካርቦን ያላቸው መጠጦች
- ሲትረስ ፍራፍሬዎች እና ጭማቂዎች
11. ራስ ምታት
በእርግዝና ጊዜ የኢስትሮጅን ሆርሞን መጠን በመጨመሩ ምክንያት ራስ ምታት ሊያጋጥም ይችላል። በተጨማሪም ውጥረት ወይም ድካም የራስ ምታት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
ሰዎች በእርግዝና ወቅት ምንም ዓይነት የራስ ምታት መድሃኒት፣ ያለ ሐኪም ማዘዣ የሚገዙ የህመም ማስታገሻዎችን ጨምሮ፣ ከመውሰዳቸው በፊት የጤና ቡድናቸውን ማማከር አለባቸው።
12. ብጉር
አንዳንድ ሰዎች ቀደም ሲልም ብጉር ቢኖራቸውም፣ በእርግዝና ወቅት ግን ሊባባስ ወይም ሊጨምር እንደሚችል ያስተውላሉ።
የአሜሪካ የጽንስና የማህፀን ሐኪሞች ኮሌጅ በእርግዝና ወቅት ብጉርን ለመቆጣጠር የሚከተሉትን ምክሮች ያቀርባል፦
- ፊትዎን በቀን ሁለት ጊዜ በቀላል ማጽጃ እና በለብ ያለ ውሃ ይታጠቡ።
- ፀጉርዎን ከፊትዎ ያርቁ።
- ዘይት የሌላቸውን (oil-free) የውበት መጠበቂያዎች ይምረጡ።
- ማንኛውንም ምርት ከመጠቀምዎ በፊት በእርግዝና ወቅት ለመጠቀም ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ከሃኪሞት ያረጋግጡ
13. የምግብ ፍላጎት መጨመርና ምግብ መጥላት
በእርግዝና መጀመሪያ ላይ ሰዎች የምግብ ፍላጎታቸው ሊለዋወጥ ይችላል። ቀደም ሲል በጣም ይወዷቸው የነበሩ ምግቦች በድንገት ሊያቅለሸልሿቸው ወይም ሊጠሏቸው ይችላሉ፣ እንዲሁም ከዚህ በፊት በፍጹም የማይወዷቸውን ምግቦች አሁን በጣም ሊመኙ ይችላሉ።
ብዙውን ጊዜ ምንም ጉዳት የማያስከትል ቢሆንም፣ አንዳንድ ጊዜ የምግብ ፍላጎት የንጥረ ነገር እጥረት አመላካች ሊሆን ይችላል።
እንደ አፈር ወይም ሳንቲሞች ያሉ የምግብ ያልሆኑ ነገሮችን የሚመኙ ከሆነ፣ "ፒካ (Pica)" የሚባል ሁኔታ ሊኖርብዎ ስለሚችል የጤና ባለሙያ ማነጋገር ይኖርብዎታል።




