የእርግዝና ሦስቱ ምዕራፎች !! ምን ይከሰታል? ለምንስ?

Elsabet Azezew
Jan 27, 2026
undefined

                                 የእርግዝና ሦስቱ ምዕራፎች !! ምን ይከሰታል? ለምንስ?

      እርግዝና ፅንስ በማህፀን ውስጥ የሚዳብርበት ወቅት ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ከወሲባዊ ግንኙነት በኋላ የሚከሰት ቢሆንም በዘመናዊ የሥነ-ተዋልዶ ቴክኖሎጂዎች (ART) አማካኝነትም ሊከሰት ይችላል። 

      እርግዝና በአማካይ 40 ሳምንታት ይቆያል። እነዚህም ሳምንታት በ 3 ምዕራፎች የሚከፈሉ ሲሆን እያንዳንዳቸውም ሦስን ወራት ወይም 13 ሳምንታት ያህል ይቆያሉ። እያንዳንዱ የእርግዝና ምዕራፍ የራሱ የሆኑ ልዩ መገለጫዎች ያሉት ሲሆን የተለያዩ ምልክቶችም በእነዚህ ወቅቶች ይታያሉ። በእነዚህ ምዕራፎች አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት እንዲሁም በማደግ ላይ ያለው ፅንስ ከፍተኛ እድገት እና ለውጥ ያሳያሉ ።   

               የመጀመሪያው የእርግዝና ምዕራፍ (The first trimester)  

የመጀመሪያው የእርግዝና ምዕራፍ ከሳምንት 1 እስከ 13 ያለውን ጊዜ የሚያካትት ሲሆን ይህም ማለት ፅንሱ ከተፈጠረበት ቀን ጀምሮ እስከ 13 ሳምንት ከ6 ቀናት ድረስ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። ይህ ወቅት ለፅንሱ እድገት እጅግ ወሳኝ ጊዜ ነው።

       ፅንሱ ላይ የሚታይ እድገት እና ለውጥ

ፅንስ በሚፈጠርበት ወቅት የሴትዋ እንቁላል እና የወንዱ የዘር ፍሬ በመዋሃድ ውሁድ ህዋስ ወይም ዛይጎት (zygote) ይፈጥራሉ ፤ ይህም በማህፀን ግድግዳ ላይ ይጣበቃል። የዛይጎቱ ህዋሳትም እየተከፋፈሉ እና እያደጉ ሲሄዱ ሽል ወይም ፅንስ (embryo) ይሆናል። 

የመጀመሪያዎቹ 12 ሳምንታት ሲጠናቀቁ ፅንሱ ላይ ብዙ ዋና ዋና እድገቶች ይስተዋላሉ ከ እነዚህ መካከል፦

  • የሰውነት ዋና ዋና የአካል ክፍሎች እና መዋቅሮች መፈጠር ይጀምራሉ
  • የልብ ምት ወጥ በሆነ መልኩ መምታት ይጀምራል
  • የእጅ እና የእግር ጣቶች ይፈጠራሉ
  • ፅንሱ ከ 7.5 - 8 ሴንቲ ሜትር ርዝመት የሚኖረው ሲሆን ክብደቱም ወደ 28 ግራም ይጠጋል
  • ነርቮች እና ጡንቻዎች አብረው መሥራት ይጀምራሉ፤ ፅንሱም እጁን መጨበጥ ይችላል
  • አይኖችን ለመጠበቅ ሲባል የዐይን ሽፋኖች ይፈጠራሉ፤ እነዚህም እስከ 28ኛው ሳምንት ድረስ እንደተዘጉ ይቆያሉ

     እናትየዋ ላይ የሚታዩ ለውጦች 

አንዲት እናት በመጀመሪያው የእርግዝና ምዕራፍ ላይ ብዙ ለውጦችን ታስተናግዳለች። እነዚህም የሚከተሉትን ያካትታሉ፦

  • ከፍተኛ ድካም
  • የጡት ህመም እና ማበጥ
  • የባህርይ መለዋወጥ
  • የአንዳንድ ምግቦች አምሮት መኖር
  • ራስ ምታት
  • የምግብ አለመፈጨት ስሜት
  • በየተደጋጋሚ ሽንት መምጣት
  • የሰውነት ክብደት ለውጥ
  • የሆድ ድርቀት
  • ማቅለሽለሽ ፤ ይህም አንዳንዴም ከማስታወክ ጋር ይከሰታል ( ቅሪት ትፋት(Morning sickness) ይባላል) 

               ሁለተኛው የእርግዝና ምዕራፍ (The second trimester)

ከሳምንት 14 እስከ 27 ያለው ጊዜ ሁለተኛው ምዕራፍ ነው። ይህም ከ 14 ሳምንት እስከ 27 ሳምንት ከ6 ቀናት ያለውን ጊዜ ያጠቃልላል። በዚህ ወቅት ፅንሱ ብዙ ለውጦችን የሚያደርግ ሲሆን ርዝመቱ 30 ሴ.ሜ ክብደቱ ደግሞ 700 ግራም ገደማ ይደርሳል። 

     በሁለተኛው ምዕራፍ መጨረሻ ላይ የሚከተሉት ለውጦች ፅንሱ ላይ ተከስተው ይጠናቀቃሉ፦

  • ሜኮኒየም (Meconium) የመጀመሪያው የፅንስ ዓይነ ምድር በፅንሱ አንጀት ውስጥ ይፈጠራል
  • ፅንሱ ማየት፣ መስማት፣ የመጥባት እንቅስቃሴ ማሳየት እና ራሱን መቧጨር ይችላል
  • ቆዳ፣ ፀጉር እና ጥፍር ይፈጠራሉ
  • ሳንባዎች ይፈጠራሉ ፤ ነገር ግን ሥራ አይጀምሩም
  • ፅንሱ ወጥ በሆነ መልኩ መተኛት እና መንቃት ይጀምራል
  • ወንድ ከሆነ የዘር ፍሬው (testicles) ወደ ከረጢቱ ይወርዳል፤ ሴት ከሆነች ደግሞ እንቁላሎቿ በእቁልጢ ውስጥ ይፈጠራሉ
  • የምላስ የጣዕም ስሜት ህዋሳት (Taste buds) ይፈጠራሉ
  • የአጥንት መቅኒ የደም ህዋሳቶችን ማምረት ይጀምራል
  • "ላኑጎ" (Lanugo) የሚባል ስስ ፀጉር የፅንሱን ሰውነት ይሸፍነዋል

     እናትየዋ ላይ 

ብዙ እናቶች በሁለተኛው የእርግዝና ምዕራፍ ላይ የተሻለ ምቾት ይሰማቸዋል። የቅሪት ትፋት (ማቅለሽለሽ) እና ድካም ብዙ ጊዜ ይቀንሳሉ ወይም ሙሉ በሙሉ ይጠፋሉ። 

በዚህ ጊዜም አዳዲስ ለውጦች ይታያሉ እነዚህም፦

  • ፅንሱ እያደገ ሲሄድ የሆድ መጠን ይጨምራል 
  • በሆድ፣ በጭን፣ በጡት እና በመቀመጫ አካባቢ የቆዳ መሰነጣጠቅ (Stretch marks) ሊታይ ይችላል
  • የጡት ጫፍ አካባቢ ያለው ቆዳ (Areola) እየጠቆረ ይሄዳል
  • በፊት ላይ የሚታይ የቆዳ ቀለም ለውጥ ወይም መጥቆር ሊከሰት ይችላል
  • ቁርጭምጭሚት፣ ጣቶች እና ፊት ሊያብጥ ይችላል
  • የቆዳ ማሳከክ ሊከሰት ይችላል። ማሳከኩ ከማስታወክ እና ከቆዳ ወይም ከዓይን ቢጫ መሆን (ጄንዲስ/Jaundice) ጋር ተያይዞ ከተከሰተ የሕክምና እርዳታ ያስፈልጎታል
  • ይህ የእርግዝና ምዕራፍ እየገፋ ሲሄድም የፅንሱን እንቅስቃሴ  መሰማት ይቻላሉ 

             ሦስተኛው የእርግዝና ምዕራፍ (The third trimester)

ሦስተኛው የእርግዝና ምዕራፍ ከ28ኛው ሳምንት ጀምሮ እስከ ወሊድ ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ነው። 

     ፅንሱ ላይ የሚታይ እድገት እና ለውጥ

በዚህ ወቅት አብዛኞቹ የአካል ክፍሎች እና የሰውነት ሥርዓቶች ተሰርተው ያለቁ ሲሆን በቀረው ጊዜም እድገታቸውን ይቀጥላሉ። በዚህ ምዕራፍ 

  • አጥንቶች እየጠነከሩ ይሄዳሉ
  • የፅንሱ እንቅስቃሴዎች ይበልጥ ጎልተው መታወቅ ይጀምራሉ
  • አይኖች ይከፈታሉ ፤ ብርሃንንም መለየት ይችላሉ
  • የሳንባ እድገት ይጠናቀቃል 
  • "ላኑጎ" የተባለው ስስ ፀጉር የሚረግፍ ሲሆን "ቨርኒክስ" (vernix) የሚባል ሰም መሰል መከላከያ ሽፋን በፅንሱ ቆዳ ላይ ይፈጠራል 
  • ወደ መውለጃ ቀኖ ሲቃረቡም ፅንሱ ወደ ሆድዎ ታችኛው ክፍል ዝቅ የሚል ሲሆን አብዛኛውም ጊዜ ራሱ ወደ ታች ያዞራል

     እናትየዋ ላይ የሚታዩ ለውጦች 

በዚህ ወቅት የፅንሱ እድገት አንዳዲስ ምቾት ማጣትን ሊያስከትል ይችላል። አንዲት እናት የሚከተሉትን ለውጦች ልታስተውልም ትችላለች :- 

  • የቃር ስሜት
  • ትንፋሽ ማጠር
  • በቁርጭምጭሚት፣ በፊት እና በጣቶች ላይ የሚታይ እብጠት
  • የእንቅልፍ እጦት
  • የባህርይ መለዋወጥ
  • ከጡት ወተት መፍሰስ 
  • ሌሎች የጡት እና የጡት ጫፍ ለውጦች
  • በተደጋጋሚ ሽንት መምጣት
  • ኪንታሮት (Hemorrhoids)
  • የውሸት ምጥ (Braxton-Hicks contractions) ፤ ይህ እውነተኛ ምጥ አይደሉም
  • እውነተኛ የምጥ መኮማተር ፤ ይህም ወሊድ መቃረቡን ያሳያል

በተጨማሪም የእርግዝናው ማብቂያ ሲቃረብ ስለ ወሊድ ሂደት እና ስለ ወላጅነት ጭንቀት (Anxiety) ሊሰማዎ ይችላል ፤ ይህም የተለመደ ነው። 

                  በእርግዝና ወቅት የሚታዩ ተፈጥሮአዊ ለውጦች ለምን ይከሠታሉ?

በእርግዝና ወቅት በጣም ብዙ የሚታዩ እና የማይታዩ አካላዊ ለውጦች እንደሚከሰቱ አይተናል። እነዚህ ተፈጥሮአዊ ለውጦች የሚኖሩት በተለያየ ምክንያት ነው። ከነዚህ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ

  1. ለእናትየው እና ለሚያድገው ፅንስ በቂ ምግብ እንዲኖር ለማድረግ፤ (ግሉኮስ፣ አሚኖ አሲድ፣ ኦክስጅን) 
  2. ከወሊድ በኋላ ለልጁ የሚሆን የጡት ወተት ለማዘጋጀት፤ 
  3. አላስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን ለማስወገድ፤ ለምሳሌ ካርቦንዳይኦክሳይድ
  4. እናት እና ልጅን ከበሽታ እና ከአደገኛ ንጥረ ነገሮች ለመጠበቅ፤ ለምሳሌ የእንግዴ ልጅ ከፅንሱ በተጨማሪ እናትየውን ከፅንሱ የወንድ ልጅ ሆርሞን ይጠብቃታል
  5. ለፅንሱ ተስማሚ የሆነ አካባቢን ለመፍጠር፤
  6. ማሕፀንን እና የዳሌ መገጣጠሚያዎችን ለምጥ እና ለወሊድ የተዘጋጁ ማድረግ ናቸው።

Comments (0)