የማህፀን ጫፍ ካንሰር (cervical cancer)

Melat Geatchew
Feb 27, 2026
undefined

የማህፀን ጫፍ ካንሰር (cervical cancer)

    ካንሰር ምንድነው?

  • ካንሰር፣ ከተለመደው የሕዋሳት አሠራር ሥርዓት ውጪ የሚራቡ እና የሚሰሩ የሕዋሳት ስብስብ ወይም ክምችት ነው። 
  • ካንሰር በአካባቢው የሚገኙትን ጤናማ ሕዋሳትን የሚያውክ ለሕይወት አስጊ የሆነ ህመም ነው፤ የጉዳቱ መጠን በካንሰሩ አይነትና በተጠቁት የሰውነት ክፍሎች ይወሰናል። 

     የማህፀን ጫፍ ካንሰር

  • የማህፀን ጫፍ ካንሰር፣ ከማኅፀን ታችኛው ክፍል ወይም ጫፍ አካባቢ የሚነሳ የካንሰር ዓይነት ነው። 
  • በዓለም የጤና ድርጅት (WHO ) ጥናት መሰረት በየዓመቱ 529‚000 የሚሆኑ ሴቶች በዚህ በሽታ ይጠቃሉ።  
  • በተጨማሪም በአፍሪካ ውስጥ በሴቶች ላይ በካንሰር ምክንያት ለሚከሰት ሞት ዋነኛ መንስኤ ነው፤ በአገራችን ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ7ሺህ በላይ ሴቶች የሚጠቁ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 6ሺህ የሚሆኑት ሕይወታቸውን ያጣሉ።   

   የማህፀን ጫፍ ካንሰርመንስኤ (Causes of cervical cancer)

  • የኤች.ፒ.ቪ (HPV) ቫይረስ ኢንፌክሽን ዋነኛው መንስኤ ሲሆን ሌሎች በውል ያልታወቁ ምክንያቶችም ሊኖሩ እንደሚችሉ ይታመናል። 
  • ኤችፒ.ቪ (HPV) ቫይረስ በሩካቤ የሚተላለፍ ሲሆን ከ 100 በላይ የተለያዩ የኤች.ፒ.ቪ ቫይረስ ዝርያዎች ይገኛሉ።
  • በአለማችን ላይ 80 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ለዚህ ቫይረስ ተጋላጭ ቢሆኑም አብዛኛውን ጊዜ ግን በካንሰሩ አይጠቁም፤ ካንሰር የሚያመጡት የቫይረሱ ዝርያዎች እጅግ ውስን ናቸው። 

የተጋላጭነት መንስኤዎች (Risk factors)

  • ከአንድ በላይ የወሲብ ጓደኛ ወይም ከአንድ በላይ የወሲብ ጓደኛ ያለው የወሲብ ወዳጅ (partners) መኖር
  • በለጋ ዕድሜ ሩካቤ መጀመር፤ ሩካቤን በአሥራዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ መጀመር
  • ኤች. አይ. ቪ ኤድስ ህመም 
  • የአባላዘር በሽታ  
  • ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ
  • ሲጋራ ማጨስ እና
  • የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም የሚቀንሱ መድኃኒቶች ናቸው።

ምልክቶቹ ምንድናቸው?

  • በመጀመሪያ ደረጃ የአለ የማኅፀን ጫፍ ካንሰር አብዛኛውን ጊዜ ምንም አይነት ምልክቶችን አያሳይም። 

   ምልክቶቹ

  • ህመም አልባ የማኅፀን ደም መድማት፣ እነዚህም
  • ከመደበኛው የወር አበባ ውጪ
  • ከሩካቤ በኋላ
  • ከማረጥ (menopause) በኋላ
  • ብልትን ከታጠቡ በኋላ ሊሆን ይችላል፡፡
  • መጥፎ ጠረን ያለው የዘንጋዳ ውሃ የመሰለ ወይም ደም የቀላቀለ የማኅፀን ፈሳሽ
  • ከሩካቤ በኋላ የሚኖር ህመም
  • የጎን፣ የወገብ ወይም የእግር ህመም
  • በሽንት ቧንቧ ወይም በፊንጢጣ መድማት
  • የእግር ማበጥ እና
  • ሽንት ወይም ሰገራ መቆጣጠር አለመቻል  (Fistula) ናቸው፡፡

ምርመራ

  • የጤና ባለሙያው የማኅፀን ጫፍ ካንሰር መኖሩን ከተጠራጠረ ከማኅፀን ጫፍ ናሙና በመውሰድ  ምርመራ ያደርጋል። 
  • በተጨማሪም የካንሰሩን ደረጃ ማወቅ ለሕክምናው ሒደት ወሳኝ ስለሆነ የተለያዩ ምርመራዎች ሊደረጉ ይችላሉ። 
  • የምስል ምርመራ   (ራጅ፣ ሲቲ ስካን፣ ኤም አር አይ) እና የደም ምርመራ ሊታዘዙ ይችላሉ።

   ሕክምናው ምንድነው ?

  • ሕክምናው በካንሰሩ ደረጃ እና በህመምተኛዋ የጤና ሁኔታ ላይ የሚወሰን ይሆናል። 
  • የአሉት የሕክምና አማራጮች ቀዶ ጥገና፣ ጨረር እና ኬሞቴራፒ ሲሆን በመጀመሪያ የህመሙ ደረጃ ላይ ለአሉ ታማሚዎቸች ቀዶ ጥገና ማድረግ ይመከራል።
  •  በአንፃሩ የህመሙ ደረጃ እየጨመረ ሲሔድ የጨረር ወይም የኬሞቴራፒ ሕክምና ማድረግ ይመከራል። አንዳንድ ጊዜ ግን ሦስቱም የሕክምና አይነቶች አንድ ላይ ተጣምረው ሊሰጡ ይችላሉ።

    እንዴት መከላከል ይቻላል ?

  • የኤች.ፒ.ቪ (HPV) ክትባት መውሰድ፤ ይህ ክትባት የማኅፀን ጫፍ እና ሌሎች ተያያዥ የካንሰር አይነቶችን ለመከላከል ያግዛል። 

          የሚሰጠው ዕድሜአቸው ከ 9-25 ዓመት ለሆናቸው እና የግብረሥጋ ግንኙነት ላልጀመሩ ልጃገረዶች ነው።

  • ሲጋራ አለማጨስ፣ የአባላዘር በሽታ እና ኤች አይ ቪ መከላከል እና መታከም 

     

    የቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግ፤ 

  • የቅድመ ካንሰር ምርመራ (Pap smear)
  • የቅድመ ካንሰር ምርመራ ወደ ካንሰርነት ሊቀየሩ የሚችሉ የማኅፀን ሕዋሳት አስቀድሞ ለመለየት እና ሕክምና ለማድረግ ያገለግላል።
  • የጤና ባለሙያው ከማኅፀን ጫፍ ናሙና በመውሰድ ምርመራ ያደርጋል፤
  • ይህ በየ3 ዓመት የሚደረግ ምርመራ ሲሆን  በዚህ ምርመራ የማኅፀን ጫፍ ካንሰር ከመከሰቱ 10 ዓመት አስቀድሞ ማወቅ ይቻላል

   ምርመራው ለነማን ይሰጣል?

  • ዕድሜያቸው ከ21 ዓመት በላይ ለሆኑ
  • ሩካቤ መፈፀም የጀመሩ
  • ከኤች አይ ቪ (HIV) ቫይረስ ጋር የሚኖሩ

    ምርመራው መቼ ሊቋረጥ ይችላል?

  • ዕድሜአቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ እና
  • ከ3 ተከታታይ ምርመራ በኋላ ምንም ችግር ካልተገኘ ምርመራው ሊቋረጥ ይችላል።
  • የኤች ፒ ቪ ዘረ-መል(HPV DNA)
  • ይህ ምርመራ ከማኅፀን ጫፍ ናሙናን በመውሰድ ለካንሰር ተጋላጭ የሚያደርጉ የቫይረስ ዓይነቶችን ለመለየት ይጠቅማል።  

Comments (0)