የማህጸን ኢንፌክሽን (Pelvic inflammatory disease/PID)

Biruh Tesfaye
Mar 6, 2026
undefined

የማህጸን ኢንፌክሽን  ወይም በህክምናው አለም ‘ፔልቪክ ኢንፍላማቶሪ በሽታ’ (Pelvic inflammatory disease/PID) ተብሎ የሚጠራው፣ በሴት የመራቢያ አካላት ላይ የሚከሰት የኢንፌክሽን አይነት ነው። በማህፀን፣ በማህፀን ቱቦዎች ወይም በእንቁልጢ (ovaries) ላይ የሚከሰት ከባድ ኢንፌክሽን ነው። ይህ ኢንፌክሽን የሚፈጠረው የተወሰኑ የባክቴሪያ ዓይነቶች ከብልት ተነስተው ወደ መራቢያ አካላት ሲሰራጩ ነው። ፒ.አይ.ዲ በአፋጣኝ ካልታከመ በመራቢያ አካላት ላይ ጠባሳ እና መግል የያዙ እብጠቶች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል፣ እነዚህም ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ የጤና ችግሮችን ያስከትላሉ።

ለማህጸን ኢንፌክሽን መከሰት ብዙ አይነት ባክቴሪያዎች መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ላልታከሙ የአባላዘር በሽታዎች ምክንያት የሚመጡ ባክቴሪያዎች ዋነኛ መንስኤዎች ናቸው። ዋነኞቹ እና በብዛት የሚታወቁት ጨብጥ (gonorrhea) እና ክላሚዲያ (chlamydia) ናቸው። እነዚህን ሁለቱንም ኢንፌክሽኖች የሚተላለፉት ጥንቃቄ በጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ነው። ከጠቅላላው የማህጸን ኢንፌክሽን ተጠቂዎች መካከል 90% የሚሆኑት ለበሽታው የተጋለጡት በእነዚህ ሁለት በግብረ ሥጋ ግንኙነት በሚተላለፉ ባክቴሪያዎች ምክንያት ነው። አንዲት ሴት በጨብጥ ወይም በክላሚዲያ ተይዛ ተገቢውን ሕክምና ካላገኘች፣ ወደ ማህጸን ኢንፌክሽን ለመቀየር ከጥቂት ቀናት እስከ ጥቂት ሳምንታት ሊወስድ ይችላል። 

የማህጸን ኢንፌክሽን በግብረ ሥጋ ግንኙነት በማይተላለፉ እንደ ባክቴሪያል ቫጂኖሲስ (BV) ባሉ የኢንፌክሽን ዓይነቶች ሊከሰት ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ በተፈጥሮ በሰውነትዎ ውስጥ የሚገኙ ባክቴሪያዎች ወደ መራቢያ አካላትዎ ውስጥ ሲገቡ ሊከሰት ይችላል። ይህ ከሚከተሉት ሁኔታዎች በኋላ ሊከሰት ይችላል፦

  • በወሊድ ወቅት።
  • በማህፀን እና በዠርባ አካባቢ በሚደረግ ቀዶ ጥገና።
  • የፅንስ መቋረጥ ካጋጠመ በኋላ።
  • በማህፀን ውስጥ የሚቀመጥ የወሊድ መከላከያ (IUD) ሲተከል። ይህ አደጋ መከላከያው በተተከለ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ብቻ የሚከሰት ነው።

ለማህጸን ኢንፌክሽን የመጋለጥ እድልን የሚጨምሩ ሁኔታዎች

ለማህጸን ኢንፌክሽን የመጋለጥ እድልዎ ከፍተኛ የሚሆነው የሚከተሉት ሁኔታዎች ካሉ ነው፦

  • ከዚህ ቀደም የአባላዘር በሽታ (STI) ከነበረብዎ
  • ከዚህ ቀደም የማህጸን ኢንፌክሽን ከነበረብዎ
  • ዕድሜዎ ከ25 ዓመት በታች ሆኖ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈጽሙ ከሆነ። በሽታው ከ15 እስከ 24 ዓመት ባሉ ሴቶች ላይ በብዛት ይታያል።
  • ከአንድ በላይ የወሲብ ጓደኛ ካለዎት ወይም ከአንድ በላይ የወሲብ ጓደኛ ካለው ሰው ጋር ግንኙነት የሚፈጽሙ ከሆነ።
  • በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት ኮንዶምን በአግባቡ አለመጠቀም።
  • የማህፀን ማጠቢያ መጠቀም (Douching)፦ የብልት ውስጥን በፈሳሽ መታጠብ ባክቴሪያዎችን ወደ መራቢያ አካላት በመግፋት ለማህጸን ኢንፌክሽን ምክንያት ሊሆን ይችላል። እንዲሁም የበሽታውን ምልክቶች ሊደብቅ ይችላል።
  • በቅርብ ጊዜ በማህፀን ውስጥ የሚቀመጥ የወሊድ መከላከያ (IUD) ተክለው ከሆነ። ለፒ.አይ.ዲ የመጋለጥ እድሉ ከፍተኛ የሚሆነው መከላከያው በተተከለ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ብቻ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ግን የመከሰት እድሉ በጣም ዝቅተኛ ነው። መከላከያው ከመቀመጡ በፊት ለኢንፌክሽን (STI) ምርመራ ማድረግ ለፒ.አይ.ዲ የመጋለጥ እድልን ይቀንሳል።

የማህጸን ኢንፌክሽን ምልክቶች 

ብዙ ሴቶች ምንም ዓይነት ምልክት ስለማይታይባቸው ፒ.አይ.ዲ (PID) እንዳለባቸው አያውቁም። ምልክቶች በሚታዩበት ጊዜም መጠነኛ ወይም በጣም ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ። ምልክቶቹ የሚከተሉትን ሊያካትቱ ይችላሉ፦

  • በታችኛው የሆድ ክፍል የሚሰማ ህመም መኖር
  • ከማህፀን የሚወጣ ከበድ ያለ ወይም ያልተለመደ ፈሳሽ መኖር፤ ፈሳሹ መጥፎ ሽታ ሊኖረው ይችላል
  • ከወር አበባ ውጭ የሚታይ ደም መፍሰስ
  • መደበኛ ያልሆነ የወር አበባ (የወር አበባ መዛባት)
  • በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት ህመም መሰማት 
  • ትኩሳት እና ብርድ ብርድ ማለት 
  • ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ
  • ቶሎ ቶሎ ሽንት መምጣት እና ሽንት በሚሸኑበት ወቅት የማቃጠል ስሜት መኖር
  • በሆድ የላይኛው ቀኝ ክፍል ላይ የሚሰማ ህመም (ይህ ብዙም አይከሰትም)

የማህጸን ኢንፌክሽን እንዴት ይመረመራል? 

የማህጸን ኢንፌክሽን በአንድ ዓይነት ምርመራ ብቻ ማረጋገጥ አይቻልም። ይልቁንም የጤና ባለሙያዎ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ በመመርኮዝ ምርመራውን ያከናውናል፦

  • የጤና ታሪክዎ፦ ይህም የእርስዎን የወሲብ ልምዶች፣ ቀደም ሲል የነበሩብዎትን በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች (STIs) እና የሚጠቀሙትን የወሊድ መከላከያ ዓይነት ያካትታል።
  • ምልክቶችዎ፦ የሚሰማዎትን ማንኛውንም ምልክት፣ ምንም እንኳ መጠነኛ ቢሆንም ለጤና ባለሙያው ይንገሩ።
  • የማህፀንና አካባቢው ምርመራ (Pelvic exam)፦ በምርመራው ወቅት ባለሙያው በማህጸ አካባቢ የህመም ስሜት ወይም እብጠት መኖሩን ይፈትሻል። እንዲሁም ከብልትዎ እና ከማህፀን በር ላይ የፈሳሽ ናሙናዎችን በጥጥ (cotton swabs) ሊወስድ ይችላል። ናሙናዎቹ የኢንፌክሽን ምልክቶችን ለመለየት ላቦራቶሪ ይላካሉ።

ሐኪምዎ ያለብዎት ችግር የማህጸን ኢንፌክሽን መሆኑን ወይም ሌላ ተመሳሳይ ምልክት ያለው በሽታ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚከተሉትን ምርመራዎች ሊያዝዙ ይችላሉ፦

  • ለአባላዘር በሽታዎች (STIs) የሚደረግ ምርመራ፦ በተለይም ለጨብጥ እና ለክላሚዲያ የሚደረግ ምርመራ። 
  • የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን (UTI) ምርመራ፦ ወይም ለሌሎች የማህጸን ህመም ሊያስከትሉ ለሚችሉ ሁኔታዎች የሚደረግ ምርመራ።
  • አልትራሳውንድ (Ultrasound) ወይም ሌሎች የምስል ምርመራዎች፦ ሐኪምዎ የውስጥ አካላትዎን በማየት የማህጸን ኢንፌክሽን ምልክቶች መኖራቸውን ለማረጋገጥ ይረዳል።
  • ሌሎች የደም እና የሽንት ምርመራዎች፦ እነዚህ ምርመራዎች ለፅንስ እና ለሌሎች በግብረ ሥጋ የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች ሊደረጉ ይችላሉ። በተጨማሪም የነጭ የደም ሴሎችን መጠን ወይም ሌሎች የኢንፌክሽን ምልክቶችን ለመለካት ያገለግላሉ።

ምርመራው አሁንም ግልጽ ካልሆነ፣ የሚከተሉት ተጨማሪ ምርመራዎች ሊያስፈልጉ ይችላሉ፦

  • ላፓሮስኮፒ (Laparoscopy)፦ በዚህ ሂደት ወቅት፣ የጤና ባለሙያው የመራቢያ አካላትን ለማየት ሲል በሆድዎ ላይ በትንሽ ቀዳዳ በኩል መብራት ያለው ቀጭን ቱቦ ያስገባል።
  • የማህፀን ግድግዳ ናሙና ምርመራ ወይም ባዮፕሲ (Endometrial biopsy)፦ በዚህ ሂደት ውስጥ፣ ባለሙያው የማህፀን የውስጠኛውን ግድግዳ (endometrial tissue) ናሙና ለመውሰድ ቀጭን ቱቦ ወደ ማህፀን ያስገባል። ናሙናው የኢንፌክሽን ምልክቶችን ለመለየት ላቦራቶሪ ውስጥ ይመረመራል።

የማህጸን ኢንፌክሽን እንዳለብዎ ከጠረጠሩ በተቻለ ፍጥነት ወደ ሐኪም ጋር መሄድ ይኖርብዎታል።

የማህጸን ኢንፌክሽን እንዴት ይታከማል?

የማህጸን ኢንፌክሽን ህክምና እንደ ምልክቶችዎ፣ እንደ ዕድሜዎ እና እንደ አጠቃላይ የጤናዎ ሁኔታ ይወሰናል። እንዲሁም እንደ በሽታው ጽኑነት (ክብደት) ሊለያይ ይችላል።

በመድኃኒት የሚደረግ ፈጣን ሕክምና ለማህጸን ኢንፌክሽን መንስኤ የሆነውን ባክተሪያ ሊያስወግድ ይችላል። ነገር ግን፣ በሽታው በመራቢያ አካላት ላይ አስቀድሞ ያደረሰውን ጠባሳ (scarring) ወይም ሌላ ጉዳት ለማስተካከል የሚያስችል መንገድ የለም። ሕክምናው አብዛኛውን ጊዜ የሚከተሉትን ያካትታል፦

  • ጸረ ባክቴሪያ መድሃኒት (Antibiotics)፦ የጤና ባለሙያዎ ወዲያውኑ የሚጀምሩትን የተለያዩ የጸረ ባክቴሪያ መድሃኒቶች ያዝልዎታል፣ አብዛኛውን ጊዜ ለ14 ቀናት የሚወሰዱ ይሆናል።። የላቦራቶሪ ውጤትዎ ሲመጣ፣ ባለሙያው ለኢንፌክሽኑ መንስኤ ከሆነው ባክቴሪያ ጋር ይበልጥ የሚሄድ ሌላ መድኃኒት ሊቀይርልዎ ይችላል። ሕክምናው እየሰራ መሆኑን ለማረጋገጥ ከሦስት ቀናት በኋላ የሕክምና ክትትል ያድርጉ። ምንም እንኳ ከጥቂት ቀናት በኋላ መሻሻል ቢሰማዎትም፣ የታዘዘልዎትን መድኃኒት በሙሉ መጨረስዎን ያረጋግጡ።
  • የወሲብ ጓደኛ ሕክምና፦ በኢንፌክሽኑ ዳግም እንዳይያዙ፣ የወሲብ ጓደኛዎ ወይም ጓደኞችዎ ምርመራና ሕክምና ሊያደርጉ ይገባል። ኢንፌክሽኑ ያለባቸው ጓደኞች ምንም ዓይነት ምልክት ላይታይባቸው ይችላል።
  • የግብረ ሥጋ ግንኙነትን ማቆም፦ ሕክምናዎን ጨርሰው ምልክቶቹ ሙሉ በሙሉ እስኪጠፉ ድረስ የግብረ ሥጋ ግንኙነት አይፈጽሙ።

ነፍሰ ጡር ከሆኑ፣ በጣም ከታመሙ፣ መግል የያዘ እብጠት (abscess) ካለብዎ ወይም በአፍ የሚወሰዱ መድኃኒቶች ለውጥ ካላመጡ ሆስፒታል መተኛት ሊያስፈልግዎ ይችላል። በዚህ ጊዜ መድኃኒቱን በደም ሥር (Intravenous) ሊያገኙ ይችላሉ፣ ከዚያም በአፍ የሚወሰዱ ይሰጥዎታል።

ቀዶ ጥገና ብዙም አያስፈልግም። ነገር ግን መግል የያዘው እብጠት (abscess) ከፈነዳ ወይም ሊፈነዳ የሚችል ከሆነ፣ የጤና ባለሙያው ፈሳሹን ሊያወጣው ይችላል። እንዲሁም በጸረ ባክቴሪያ ሕክምና መዳን ካልቻሉ ቀዶ ጥገና ሊያስፈልግ ይችላል።

ያለ ህክምና የማህጸን ኢንፌክሽን እንደ መካንነት፣ ከማህፀን ውጭ የሚፈጠር እርግዝና እና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ (የማይለቅ) የማህጸን ህመም ያሉ ከባድ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል።

የማህጸን ኢንፌክሽን መከላከያ መንገዶች

  • ኮንዶም ይጠቀሙ፦ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት ለበሽታ የመጋለጥ እድልን ለመቀነስ ኮንዶም ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው። እንደ የወሊድ መከላከያ ክኒኖች፣ መርፌዎች፣ የሚቀበሩ መከላከያዎች ወይም ዲያፍራም ያሉ ሌሎች የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች ከኢንፌክሽን (STIs) አይከላከሉም።
  • ይመረመሩ፦ እርስዎም ሆኑ የትዳር/የወሲብ ጓደኛዎ ለአባላዘር ኢንፌክሽኖች መመርመራችሁን ያረጋግጡ። 
  • የወሲብ አጋርዎን ቁጥርን ይገድቡ፦ የወሲብ ጓደኞች ቁጥር በበዛ ቁጥር ለኢንፌክሽን የመጋለጥ እድልዎም አብሮ ይጨምራል።
  • ብልትን በውስጥ በኩል አይጠቡ (Avoid Douching)፦ ብልትን በፈሳሽ መታጠብ ከኢንፌክሽን የሚከላከሉ ተፈጥሯዊ ባክቴሪያዎችን ያስወግዳል። በተጨማሪም ባክቴሪያዎች ወደ ማህፀን እንዲጓዙ በማገዝ ለኢንፌክሽኑ የመጋለጥ እድልን ይጨምራል።
  • አልኮልን ወይም አደንዛዥ ዕፅን አያዘወትሩ፦ ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት ወይም አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም ለአደገኛ ባህሪያት ያጋልጣል፤ ይህም ለጾታዊ ጥቃት እና ለአባላዘር በሽታዎች ተጋላጭ ሊያደርግዎ ይችላል።
  • ምልክቶች ሲታዩ ወደ ሕክምና ይሂዱ፦ የማህጸን ኢንፌክሽን ወይም የአባላዘር በሽታ ምልክቶች ካዩ ወዲያውኑ ሕክምና ያግኙ። 

Comments (0)