ጤናማ ያልሆነ የሴት ብልት ፈሳሽ (Abnormal Vaginal discharge)

Melat Geatchew
Mar 12, 2026

ጤናማ ያልሆነ የሴት ብልት ፈሳሽ (Abnormal Vaginal discharge)

የሴት ብልት ፈሳሽ ምንድነው?

  • ይህ ከሴት ብልት የሚወጣ የፈሳሽ፣ የሕዋሳት እና የንፋጭ ጥምረት ሲሆን የሴት ብልት አካሎችን ከበሽታ እና ከብግነት በመከላከል የሴት ብልት አካሎች ጤናማ እዲሆኑ ያደርጋል። 

የሴት ብልት ፈሳሽ እንዴት ይፈጠራል?

  • የሴት ብልት ፈሳሽ በዋነኝነት በሴት ሆርሞን (ኢስትሮጂን) አማካኝነት በብልት እና በማህጸን ሽፋን ሕዋሳት ይሠራል ፡፡ 

-ባልአረጡ ሴቶች የሚኖር ጤናማ የሴት ብልት ፈሳሽ ይዘት

  • መጠን፤ በግምት በየቀኑ ከአንድ እስከ ግማሽ የሻይ ማንኪያ (ከ 2 እስከ 5 ሚ.ሊ ) 
  • ቀለም፤ ነጭ ወይም ደፍረስ ያለ ነጭ 
  • ይዘት፤ ቀጭን ወይም ወፈር ብሎ እንደ ንፍጥ ያለ ፈሳሽ ሊሆን ይችላል። 
  • ሽታ፤መጠነኛ ሽታ ወይም ሽታ አልባ ሊሆን ይችላል ፡፡

- የሴት ብልት ፈሳሽ ይዘት፣ መጠን እና ቀለም በእርግዝና፤ በወር አበባ ዑደት ደረጃ እና በሆርሞን የወሊድ መቆጣጠሪያ መድኃኒቶች መሰረት የሚለያይ ሲሆን ይዘቱ ነጭ የሚያጣብቅ እስከ ንፁህ እና ውሃማ ሊቀያየር ይችላል ፡፡ ይህ ፈሳሽ የሽንት ቧንቧን ከኢንፌክሽን ይከላከላል፤ በተጨማሪም እንደቅባት በመሆን የሴት ብልትን በማለስለስ ብግነትን ይቀንሳል።

-በአጠቃላይ የአረጡ ሴቶች ዝቅተኛ የኢስትሮጅን መጠን ስለሚኖራቸው  አነስተኛ የሴት ብልት ፈሳሽ ይኖራቸዋል፡፡

 

ያልተለመደ የሴት ብልት ፈሳሽ

ያልተለመደ የሴት ብልት ፈሳሽ ምልክቶች ምንድናቸው? 

  • የብልት ማሳከክ፣ ማቃጠል፣ መቅላት፣ እብጠት ወይም ህመም መኖር  
  • የብልት ፈሳሽ አረፋማ መሆን ወይም ቀለሙ መቀየር (መወየብ፣ አረንጓዴ መሆን)   
  • ከባድ ሽታ   
  • ደም የቀላቀለ ፈሳሽ
  • ከግብረሥጋ ግንኙነት ወይም ከሽንት በኋላ ህመም መኖር
  • የሆድ ወይም የወገብ ህመም።

ያልተለመደ የሴት ብልት ፈሳሽ መንስኤዎቹ ምንድናቸው?

  • ኢንፌክሽን 
  • የሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን ( የሴት የመራቢያ አካላት የፈንገስ ኢንፌክሽን) እና
  • ፣ ባክቴሪያል ቫጂኖሲስ ፣ ትሪኮማናስ፤ እነዚህ በአንፃሩ ቀለል ያሉ ኢንፌክኖች ናቸው።
  • የአባላዘር በሽታ፤ ይህ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፍ ኢንፌክሽን (STIs) ሲሆን ማኅፀን፣ እንቁልጢን እና የማኅፀን ቱቦዎች ጨምሮ ሊያጠቃ ይችላል። 
  • በማኅፀን ውስጥ የተረሱ ባእድ ነገሮች (ታምፖን፣ ኮንዶም) ወይም የወንድዘር ፍሬን የሚገድሉ ቅባቶችን መጠቀም ለኢንፌክሽን ሊዳርግ ይችላል።

 ሌሎች መንስኤዎች

  • አንዳንድ የንፅህና አጠባበቅ ዘይቤዎች፤ ለምሳሌ ሳሙና ወይም የንፅህና መጠበቂያ በመጠቀም ማኅፀንን ማፅዳት 
  • የማኅፀን ጫፍ ካንሰር
  • እርግዝና
  • ከማረጥ በኋላ የሚከሰቱ የሴት ብልት ለውጦች፤ ይህም የሴት ብልት ድርቀት፣ በተለይም ከግብረሥጋ ግንኙነት በኋላ የብልት ፈሳሽ መቀየር ናቸው። 
  • የሴት ብልት ካንሰር፣ ቧንቢት (Fistula)

ጤናማ ያልሆነ የሴት ብልት ፈሳሽ ምርመራ

  • በምርመራ ወቅት የጤና ባለሙያው ምልክቶቹን ይጠይቃል፤ የአካላዊ እና የማኅፀን ምርመራ ጨምሮ ያደርጋል። እዲሁም ከፈሳሹ ናሙና በመውሰድ ምርመራ ሊያደርግ ይችላል። 
  • አስፈላጊ ከሆነ የአልትራሳውንድ ምስል ምርመራ ሊደረግ ይችላል።

ሕክምና

  • በዋነኝነት የሕክምና እና የመከላከያ መንገዶች ህመሙን ባመጣው መንስኤ ላይ የሚወሰን ይሆናል። 
  • የሚከተሉት ሕክምናዎች አብዛኛውን ጊዜ በወጣት ሴቶች ላይ ለሚከሰት ጤናማ ያልሆነ የብልት ፈሳሽ  የሚሰጡ ሕክምናዎች ናቸው። 
  • መንስኤው የፈንገስ ወይም የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ የፀረ ፈንገስ እና አንቲባዮቲክስ መድኃኒቶች ከምርመራ በኋላ ወዲያውኑ እዲጀመሩ ይደረጋል። 
  • በግብረሥጋ ግንኙነት የሚተላለፍ የአባላዘር በሽታ ከሆነ መንስኤው አንቲባዮቲክስ መድኃኒት የሚታዘዝ ሲሆን በተጨማሪም የትዳር አጋር እዲታከም ይደረጋል።

በቤት ውስጥ የሚደረግ ሕክምና

  • ረጠብ እና ቀዝቀዝ ያለ ጨርቅ ማድረግ፤ ይህም የብልት ማሳከክ፣ ማቃጠል ወይም ምቾት ማጣትን ይቀንሳል። 
  • በግብረሥጋ ግንኙነት ወቅት ኮንዶም መጠቀም፤ ይህ ሕክምና ከተጀመረ በኋላ እስከ አንድ ሳምንት ድረስ ቢቀጥል ይመከራል።
  • ብልትን ለማፅዳት ውሃ ወይም ከሳሙና ነፃ የሆኑ ማጽጃዎችን መጠቀም፣ ሞቅ ያለ ውሃ ቢሆን ይመረጣል፤ ለማፅዳት ጨርቅ ከመጠቀም ይልቅ በእጅ ቢሆን ይመረጣል።
  • ከጥጥ የተሰሩ የውስጥ ሱሪዎችን መጠቀም እና
  • ጥሩ መዓዛ የአላቸው የንፅህና ምርቶችን የሕፃናት መጥረጊያዎችን ጨምሮ(wipes) አለመጠቀም ናቸው።
  • በተጨማሪም ምልክቶቹ እየባሱ ከሔዱ ሐኪም ማማከር ያስፈልጋል።  

Comments (0)