የሴት መራቢያ አካላት የፈንገስ ኢንፌክሽን (Vaginal yeast infection)

Melat Geatchew
Mar 12, 2026
undefined

የሴት መራቢያ አካላት የፈንገስ ኢንፌክሽን (Vaginal yeast infection)

  • ጥናቶች እደሚያሳዩት ከሆነ አንዲት ሴት በህይወት ዘመኗ ቢያንስ አንድ ጊዜ የመራቢያ አካላት የፈንገስ ኢንፌክሽን ሊያጋጥማት ይችላል። ይህ ችግር የወር አበባ ማየት የጀመሩ ሴቶች ላይ የተለመደ ሲሆን የወር አበባ ማየት በአልጀመሩ ሴቶች እና በአረጡ ሴቶች የመከሰት እድሉ አነስተኛ ነው።

ይህ የፈንገስ ኢንፌክሽን እንዴት ይከሰታል?

  • ይህ 90 ከመቶ የሚሆነው የሴት ብልት ኢንፌክሽን ካንዲዳ አልቢካንስ(Candida albicans) በሚባለው የፈንገስ ዝርያ አማካኝነት ይከሰታል። ይህ የፈንገስ ዝርያ በሰውነታችን ውስጥ በጥገኝነት የሚኖር ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች የሰውነታችን በሽታ የመከላከል አቅም ሲዳከም ኢንፌክሽን ሊያስከትል የሚችል ነው።
  • ይህ ፈንገስ በግንኙነት የማይተላለፍ ቢሆንም ንቁ የሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ህይወት በሚመሩ ሴቶች ላይ ግን በብዛት ይስተዋላል።የሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን የሚያመጣው ፈንገስ አብዛኛውን ጊዜ በአንጀት ውስጥ እና በሴት ብልት ውስጥ ይኖራል። ይሁንና የፈንገሱ ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ አብዛኛውን ጊዜ የበሽታ ምልክቶች አይኖርም።
  • የተወሰኑ መድሃኒቶች (በተለይም አንቲባዮቲክስ) ፣ ጭንቀትና ሌሎች ምክንያቶች ፈንገሶቹ እንዲባዙ ሊያደርጉ ይችላሉ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ የማህጸን የፈንገስ ኢንፌክሽን ምልክት መታየት ይጀምራ።

ለፈንገስ ኢንፌክሽን የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ምንድናቸው?

  • የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም መቀነስ፤ ለምሳሌ ኤች አይ ቪ ኤድስ ህመም፣ አንዳንድ መድኃኒቶች(Steroids)
  • የስኳር ህመም
  • እርግዝና 
  • ከኢስትሮጅን ሆርሞን የተሰሩ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች
  • መድኃኒቶች (antibiotics)
  • ከመጠን ያለፈ ውፍረት
  • ለረዥም ጊዜ የቆየ ህመም(chronic disease)

 

ምልክቶቹስ ምንድናቸው?

አብዛኛዎቹ ሴቶች የምልክታቸው መንስኤ የሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን ይሁን ወይም ሌላ ነገር ይሁን ሊያውቁ አይችሉም ። የሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን ምልክቶች ከሌሎች የሴት ብልት ኢንፌክሽን ምልክቶች ጋር ተመሳሳይ ናቸው ፤ ስለዚህ ምርመራ ሳያደርጉ በዚህ ምክንያት ነው ብሎ ለመናገር በጣም አስቸጋሪ ነው። እርግጠኛ ለመሆን ሃኪም ወይም ነርስጋ ቀርቦ መታየት እና ከማህጸን ፈሳሽ ናሙና ተወስዶ የላቦራቶሪ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል። 

  • ማሳከክ፣ ማቃጠል
  • የሴት ብልት እና የሴት ብልት የውጨኛው ቆዳ ማቃጠል፣ መቅላት ወይም መቆጣት
  • አይብ የሚመስል ወፍራም የብልት ፈሳሽ መኖር (ሽታ ሊኖረው ይችላል)
  • የሽንት ማቃጠል እና
  • በግንኙነት ሰዓት ህመም መሰማት ናቸው።

ምርመራ

  • የጤና ባለሙያው ምልክቶቹን በመጠየቅ እና የማኅፀን ምርመራ በማድረግ ስለህመሙ ለመረዳት ይሞክራል። በተጨማሪም ከማኅፀን ፈሳሽ ናሙና በመውሰድ የፈንገስ ምርመራ ያደርጋል።

ሕክምናው ምንድነው?

መንስኤዎቹን መቆጣጠር። እነዚህም

  • የስኳር ህመም መታከም እና መቆጣጠር እዲሁም ሌሎች ሕመሞች ከአሉ በአግባቡ መታከም
  • የሰውነት ክብደትን ጤናማ ማድረግ እና
  • ያለሐኪም ትዕዛዝ መድኃኒት አለመውሰድ ናቸው። 

መድኃኒቶች

  •  ለሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን የሚሆኑ መድኃኒቶች ​​ሊወስዱ ይችላሉ።እነዚህ የፀረ ፈንገስ መድኃኒቶች ሲሆኑ የሚቀቡ፣ በማህጸን የሚገቡ፣ የሚዋጡ ወይም የተቀመሙ መታጠቢያ ሊሆኑ ይችላሉ። መድኃኒቶች የሚዋጡ ወይም በሴት ብልት ውስጥ የሚቀመጡ ሊሆኑ ይችላሉ። በሴት ብልት ውስጥ የሚቀመጡት መድሃኒቶች በክኒን ወይም በክሬም መልክ ሊመጡ ይችላሉ። ለሴት ብልት የፈንገስ ኢንፌክሽን የሚወሰዱ ሁሉም መድሃኒቶች ኢንፌክሽኑን የሚያስከትሉ ፈንገሶችን በመግደል ይሰራሉ። 
  • ሕክምና እንደጀመሩ በጥቂት ቀናት ጊዜ ውስጥ ጥሩ ስሜት ሊሰማዎት ይችላል። ህክምናን ካጠናቀቁ በኋላ ካልተሻለዎት ​​ዶክተርዎን ወይም ነርስዎን እንደገና ማየት አለብዎት ፤ ተጨማሪ መድሃኒት መውሰድ ወይም ሌላ መድሃኒት መውሰድ ይኖርብዎት ይሆናል።

እንዴት መከላከል ይቻላል? 

  • የታወቀ እና የቆየ ህመም ከአለ መታከም (ለምሳሌ ስኳር ህመም፣ኤች አይ ቪ ኤድስ)
  • ከአለሐኪም ትዕዛዝ መድኃኒትን አለመውሰድ
  • የሚጠቀሙትን የወሊድ መከላከያ ዘዴ መቀየር ከአስፈለገ ከሐኪም ጋር መማከር
  • ከተቻለ ከጥጥ የተሰሩ የውስጥ ሱሪ መጠቀም
  • ንፅህናን ለመጠበቅ ውሃ ብቻ መጠቀም እና
  • በጭን መሃል የሚፈጠረውን ሙቀት ለመቀነስ ሱሪ(አጠር ያለ ሱሪ ወይም ታይት ሊሆን ይችላል) መጠቀም ናቸው።

 



 

Comments (0)