ጡት ማጥባት ሰውነትዎ ያመነጨውን ወተት ለሕፃኑ የመመገብ ሂደት ነው። አብዛኛውን ጊዜ ሕፃናት እንደተወለዱ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሰዓታት ውስጥ ጡት መጥባት ይጀምራሉ።
የጡት ወተት ለሕፃናት ተመራጭና ተስማሚ ምግብ ነው። ንጹሕና ደህንነቱ የተጠበቀ ከመሆኑም በላይ፣ ሕፃናትን ከተለመዱ የልጅነት ሕመሞች የሚከላከሉ ንጥረ ነገሮችን (antibodies) ይዟል። የጡት ወተት አንድ ሕፃን በመጀመሪያዎቹ ጥቂት የሕይወት ወራት ለሚያስፈልገው ዕድገት ሙሉ ኃይልንና ንጥረ ነገሮችን (nutrients) ያቀርባል። መጀመሪያ ላይ፣ ሰውነትዎ ኮለስትረም (colostrum) የተባለ የመጀመሪያውን የወተት ዓይነት ያመነጫል። ይህ ወተት በፕሮቲን የበለፀገ እና ወፈር ያለ ፈሳሽ ነው። ጡት ማጥባት ከጀመሩ ከሦስት እስከ አምስት ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ፣ ይህ የመጀመሪያ ወተት ወደ መደበኛው ወተትነት ይቀየራል። በዚህ የሽግግር ወቅት ሕፃኑ መጠነኛ የሰውነት ክብደት ሊቀንስ ይችላል።
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ጡት የሚጠቡ ሕፃናት በፈተናዎች ላይ የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ፤ እንዲሁም ለከፍተኛ ውፍረት (obesity) የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ ነው። በተጨማሪም፣ በኋለኛው የሕይወት ዘመናቸው ለስኳር በሽታ የመጋለጥ እድላቸው የቀነሰ ነው። በተጨማሪም ጡት የሚጠቡ ሕፃናት ለሚከተሉት የጤና ችግሮች የመጋለጥ እድላቸው ዝቅተኛ ነው፦
- አስም
- ከባድ የመተንፈሻ አካላት በሽታ፦ ለምሳሌ እንደ የሳንባ ምች ያሉ በሽታዎች።
- ዓይነት 1 ስኳር በሽታ
- አጣዳፊ ጆሮ ኢንፌክሽን
- ድንገተኛ የሕፃናት ሞት
- የጨጓራና አንጀት ኢንፌክሽኖች፦ ተቅማጥ እና ማስመለስን የሚያስከትሉ የሆድ ውስጥ ህመሞች።
- የአንጀት መበስበስ (NEC)፦ ይህ ችግር ያለጊዜያቸው ለተወለዱ ሕፃናት የሚያጋጥም ሲሆን፣ የአንጀት ሕብረ ሕዋስ እንዲሞት የሚያደርግ ከባድ የጤና እክል ነው።
- በጎልማሳነት ዕድሜ የሚከሰት የልብ በሽታ
ጡት ለሚያጠቡ እናቶችም በተመሳሳይ የትለያዩ ጥቅሞችን ይሰጣል። ከነዚህም መካከል ከወሊድ በኋላ የሰውነት ክብደትን ለመቀነስ ይረዳል፣ የመውለድ አቅምን ያዘገያል፣ የእናትየውን በራስ መተማመን ይጨምራል እንዲሁም ከልጁ ጋር የጠበቀ ትስስር እንዲፈጠር ያደርጋል። ጡት ማጥባት የእናቶችን ለሚከተሉት የጤና ችግሮች የመጋለጥ እድል ለመቀነስ ይረዳል፦
- ከፍተኛ የደም ግፊት
- የዓይነት 2 ስኳር በሽታ
- የጡት እና የእንቁልጢ (ovarian) ካንሰር
- ከወሊድ በኋላ ለሚከሰት የድብርት ስሜት (postpartum depression)
- የአጥንት መሳሳት
- የልብ በሽታ
ጡት በሚያጠቡ ጊዜ ማወቅ ያለብዎት ነገሮች
በወለዱ በመጀመሪያው አንድ ሰዓት ውስጥ ጡት ያጥቡ
አዲስ የተወለደውን ሕፃን በተወለደ በአንድ ሰዓት ውስጥ ጡት ማጥባት ሕፃኑ የመትረፍ እና የተሻለ ዕድገት የማግኘት ዕድሉን ከፍተኛ ያደርገዋል። የጡት ወተት ለሕፃኑ የመጀመሪያው ክትባት ሲሆን፣ አደገኛ ከሆኑ በሽታዎች የመከላከል አቅምን (Immunity) ይጨምራል። ጥቂት ሰዓታትን እንኳ ዘግይቶ ማጥባት ለአራስ ሕፃናት ለሕይወት አስጊ የሆኑ አደጋዎችን ሊያስከትል ይችላል፤ እንዲሁም እናቲቱ ጡት የማጥባት ብቃቷ እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል።
ሕፃኑን እስከ 6 ወር እስኪሞላው ድረስ በጡት ወተት ብቻ ይመግቡ
ሕፃኑ ከተወለደበት የመጀመሪያው ሰዓት ጀምሮ እስከ 6 ወር ዕድሜው ድረስ የሚያስፈልገውን የተሟላ የአመጋገብ ይዘት ከጡት ወተት ብቻ ማግኘት ይችላል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከጡት ወተት ውጭ ሌላ ምንም ዓይነት ምግብም ሆነ መጠጥ ውኃን ጨምሮ አያስፈልገውም።
ሕፃኑ 6 ወር ሳይሞላው ከጡት ወተት ውጭ ሌሎች ምግቦችን ወይም መጠጦችን መስጠት ለተቅማጥ እና መሰል በሽታዎች የመጋለጥ ዕድሉን ይጨምራል። ይህም ሕፃኑ እንዲከሳ፣ እንዲዳከም እና ለሕይወት አስጊ ለሆነ አደጋ እንዲጋለጥ ሊያደርገው ይችላል። ሕፃኑ 6 ወር ሲሞላው ከጡት ወተት በተጨማሪ ለስላሳ ምግቦችን መጀመር ይችላሉ፤ ሆኖም ጡት ማጥባቱን እስከ 2 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ መቀጠል ይኖርባቸዋል።
ሕፃኑ በአግባቡ ጡት መያዙን ያረጋግጡ
ጡት ማጥባት ለእርስዎም ሆነ ለሕፃኑ ምቹ እንዲሆን ትክክለኛ የጡት አያያዝ ወሳኝ ነው። ሕፃኑን ከእርስዎ አካል ጋር ምንም ዓይነት ክፍተት እንዳይኖር አድርገው "ሆድ ለሆድ" (tummy to tummy) ማቀፍ ይኖርብዎታል። ሕፃኑ ፊቱን በቀጥታ ወደ ጡትዎ ማዞር አለበት። የሕፃኑን የራስ ቅል የኋላ ክፍል እንዳይጫኑ ጥንቃቄ ያድርጉ።
ሕፃኑ ጡት በአግባቡ መያዙን የሚያሳዩ ምልክቶች መካከል የሚከተሉት ያጠቃልላሉ፡
- ምንም ዓይነት የሕመም ስሜት የሌለበትና ምቹ የሆነ ጡት የማጥባት ሂደት መኖር
- ከሕፃኑ አፍ በላይ ያለው የጡት ጥቁር ክፍል (Areola) ከታች ካለው በበለጠ ታይቶ መታየት
- የሕፃኑ አፍ በደንብ ተከፍቶ መታየት
- የሕፃኑ የታችኛው ከንፈር ወደ ውጭ ተገልብጦ መታየት
- የሕፃኑ አገጭ ጡትዎን ነክቶት ወይም ሊነካው ተቃርቦ መታየት
ሕፃኑ ጡት በአግባቡ እንዳልያዘ የሚያሳዩ ምልክቶች፦
- ጡት በሚያጠቡበት ጊዜ የጡት ጫፍዎ መቁሰል፣ መሰንጠቅ ወይም ደም መፍሰስ ከጀመሩ
- ሕፃኑ ጡቱን ሲለቅ የጡትዎ ጫፍ የታጠፈ ወይም የተዛባ ቅርጽ ካለው
- ሕፃኑ በሚጠባበት ጊዜ የመመጥመጥ ድምፅ የሚሰማ ከሆነ
- ሕፃኑ ጥቂት ከጠባ በኋላ ደጋግሞ ጡቱን የሚለቅ ከሆነ
- ሕፃኑ በሚጠባበት ጊዜ ጉንጮቹ ወደ ውስጥ የሚጎድጉዱ (dimpling) ከሆነ።
- ሕፃኑ ከጠባ በኋላም ቢሆን ሁልጊዜ የራብ ስሜት የሚያሳይ ከሆነ።
- ሕፃኑ በቀን ከ 6 እስከ 8 ያነሰ የራሰ የሽንት ጨርቅ/ዲያፐር ካለው።
ሕፃኑ በፈለገበት ጊዜ ያጥቡት
የሕፃኑ ፍላጎትና የራብ ስሜት ሁልጊዜ ተለዋዋጭ ነው። ስለዚህ ንቁ በመሆን ሕፃኑ የራብ ምልክቶችን ባሳየ ቁጥር ጡት ያጥቡት። ሕፃኑ በፈለገው ቁጥር፣ በቀንም ሆነ በሌሊት ያጥቡት። ጡት ለማጥባት የተወሰነ የጊዜ ሰሌዳ ለመጠቀም አይሞክሩ። ይልቁንም ሕፃኑ መቼ መጥባት እንዳለበትና ለምን ያህል ጊዜ መጥባት እንደሚፈልግ እራሱ እንዲወስን ይፍቀዱለት።
ጡት በማጥባት ላይ እያሉ ጡጦ እና የእንጀራ እናት ጡጦ (pacifiers) ከመጠቀም ይቆጠቡ። ሕፃኑን ለማባበል ጥሩ ቢሆኑም፣ ሕፃኑ ጡት መጥባትን ያለጊዜው እንዲያቆም ሊያደርጉት ይችላሉ።
መጀመሪያ የሞላውን ጡትዎን በማጥባት ይጀምሩ፤ ሕፃኑ ራሱ የጡት ጫፉን እስኪለቅ ድረስ ያጥቡት። ከዚያም ሕፃኑን እንዲያገሳ ካስደረጉት በኋላ ሌላኛውን ጡትዎን ይስጡት። አንዳንድ ሕፃናት በአንድ ጊዜ ከሁለቱም ጡቶች ሊጠቡ ይችላሉ፤ ሌሎች ደግሞ በአንዱ ብቻ ሊረኩ ይችላሉ። ጡቶችዎ መሙላት ሲጀምሩ ሕፃኑን ማጥባት በጣም አስፈላጊ ነው፤ ይህም ጡትዎ ከመጠን በላይ እንዳይወጠር ወይም እንዳያብጥ ይረዳል።
ጡት በሚያጠቡበት ጊዜ ሕፃኑ እንዳይተኛ ማድረግ
በተለይም በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት ሕፃናት ጡት እየጠቡ መተኛታቸው የተለመደ ነው። ነገር ግን ሕፃኑ ወዲያው የሚተኛ ከሆነ በቂ ወተት እንዳያገኝ ሊያደርገው ይችላል። ሕፃኑ ነቅቶ እንዲጠባ ማድረግ በቂ ምግብ እንዲያገኝ ከመጥቀሙም በላይ፣ ጥሩ የእንቅልፍ ልምድ እንዲያዳብር (ምግብን ከእንቅልፍ ጋር ብቻ እንዳያያዝ) ይረዳል።
ሕፃኑ እንዳይተኛ የሚረዱ መንገዶች፦
- እግሮቻቸውን ወይም እጆቻቸውን በቀስታ መነካካት።
- ሕፃኑ እንቅልፍ ሲጭነው ጡት የሚያጥቡበትን አቀማመጥ መቀየር ወይም ወደ ሌላኛው ጡት ማዛወር።
- ለሕፃኑ መዘመር ወይም ማውራት።
በቂ ፈሳሽ እና ውኃ ይጠጡ
ጡት በማጥባት ወቅት ሰውነትዎ ከፍተኛ መጠን ያለው ፈሳሽ ያጣል። ስለዚህ የሰውነትዎን የፈሳሽ መጠን ለመጠበቅ የሚጠጡትን የውኃ መጠን መጨመር በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ሰውነትዎ በቂ ወተት እንዲያመርትም ይረዳል። በቀን ከ 8-10 ብርጭቆ ውኃ እንዲጠጡ ይመከራል። ውኃ ለሰውነትዎ ተመራጭ ቢሆንም፣ ወተት እና ንጹህ የፍራፍሬ ጭማቂዎችንም መጠጣት ይችላሉ።
የጡት ወተትን አልቦ ማስቀመጥ
ሁልጊዜ ሕፃኑን በደረትዎ አቅፈው ለማጥባት ላይመችዎት ይችላል። የጡት ወተትን በእጅ ወይም በማለቢያ መሣሪያ (pump) አልቦ ማከማቸት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ለሕፃኑ ለመስጠት ይረዳል። በተለይ ወደ ሥራ ከተመለሱ፣ ወተት አልቦ ማስቀመጥ ጡትዎ ወተት ማምረቱን እንዲቀጥል ይረዳዋል።
ወተት ሲያልቡ ማስታወስ የሚገቡዎት ነጥቦች፦
- ወተት ከማለብዎ በፊት ሁልጊዜ እጅዎን በሳሙና ይታጠቡ።
- በንጹሕ ዕቃ አልበው በክዳን ይዝጉት።
- የታለበ ወተት በቤት ውስጥ ባለው ሙቀት (Room temperature) ከ 4-6 ሰዓታት፣ በፍሪጅ ውስጥ (refrigerator) ውስጥ ደግሞ ከ4 እስከ 5 ቀናት ሊቆይ ይችላል።
የተለመዱ የጡት ማጥባት አቀማመጦች
ጡት በሚያጠቡበት ጊዜ ልጅዎን ለመያዝ የሚያስችሉ ብዙ መንገዶች አሉ። ከነዚህም መካከል
- ጋደም ብሎ ማጥባት (Laid Back)፦ ጀርባዎን ደገፍ አድርገው በደንብ ጋደም ይበሉ። ልጅዎ ሆድ ለሆድ ተጋጥሞ ወደ እርስዎ ዞሮ ይተኛል፤ አፉም ከጡትዎ ጫፍ ላይ ይሆናል። ይህ አቀማመጥ ጡት መጥባትን ለሚለማመዱ ህጻናት ጥሩ ነው።
- እቅፎ ማጥባት (Cradle Hold)፦ ልጅዎን በሆድዎ ላይ አጋድመው ይያዙ፤ ራሱን በክርንዎ መታጠፊያ ላይ ያሳርፉ። እርስዎ እና ልጅዎ ሆድ ለሆድ መገጣጠም አለባችሁ። በሌላኛው እጅዎም ልጅዎን መደገፍ ይችላሉ።
- በጎን በኩል መያዝ (Side Hold/Football Hold)፦ ልጅዎን በጎንዎ በኩል በትራስ ላይ ያስቀምጡት፤ ከዚያም በአንድ እጅዎ ራሱን ወደ ጡትዎ ያስጠጉት። ይህ አቀማመጥ ለትናንሽ ህጻናት ወይም በኦፕሬሽን (C-section) ለወለዱ እናቶች አመቺ ነው።
ልጄ ምን ያህል ወተት ያስፈልገዋል?
የሕፃናት ሆድ በጣም ትንሽ ነው። ስለዚህ ቶሎ ሊጠግቡ ቢችሉም፣ በተደጋጋሚ መመገብ ይኖርባቸዋል፦ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከ8 እስከ 12 ጊዜ ማጥባት ይገባዎታል። ለምግብ የሚሆን የተወሰነ ሰዓት የለም፤ በአንድ ጡት ለ15-20 ደቂቃዎች ሊሆን ይችላል፤ አንዳንዴ ደግሞ ከዚያ ሊያጥር ወይም ሊረዝም ይችላል። ሕፃኑ ጠጥቶ ሲጨርስ ራሱ ምልክት ይሰጥዎታል። የሕፃኑ የአመጋገብ ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን ሊቀያየር ስለሚችል፣ የሕፃኑን ፍላጎት ብቻ ያስተውሉ።
ሕፃኑ በቂ ወተት እያገኘ መሆኑን እንዴት ማወቅ ይቻላል? አንዱ ቀላሉ መንገድ የሕፃኑን ዓይነ ምድር እና ሽንት መከታተል ነው። የሰገራ ቀለም፣ ይዘት እና የዲያፐር መርጠብ ብዛት ብዙ መረጃ ይሰጥዎታል።
ሕፃኑ በቂ ወተት እያገኘ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች፦
- በ24 ሰዓታት ውስጥ ቢያንስ ስምንት ጊዜ ጡት ይጠባል።
- ለ10 ደቂቃ ወይም ከዚያ በላይ በሆነ ወጥ የሆነ የ"መጥባት/መዋጥ/ማረፍ/መጥባት" ሂደት ይጠባል።
- ከጠባ በኋላ ይረካል፤ እንዲሁም የረሃብ ምልክቶችን (ለምሳሌ ጡት መፈለግ ወይም ጣቶቹን መጥባት) አያሳይም።
- በተወለደ በመጀመሪያው ቀን 1 የራሰ ጨርቅ (diaper)፣ በ2ኛው እና 3ኛው ቀን 3 የራሰ ጨርቅ፣ በ4ኛው እና 5ኛው ቀን ደግሞ ቁጥሩ ይጨምራል። ከ6ኛው ቀን ጀምሮ በቀን ቢያንስ ከ6-8 የራሰ ጨርቅ ይኖረዋል።
- እስከ 5ኛው ቀን ድረስ ለስላሳ እና ቢጫ መሰል ሰገራ ያሳያል።
- የሰውነት ክብደት ይጨምራል። ሕፃኑ በተወለደ በመጀመሪያው ሳምንት ውስጥ ክብደቱ መለካት አለበት። ጡት የሚጠቡ ሕፃናት ወተት መምጣት በሚጀምርበት ከ4-5ኛው ቀን አካባቢ ክብደት መቀነሳቸውን ያቆማሉ። አብዛኛውን ጊዜ በ2 ሳምንት ዕድሜያቸው ወደ ተወለዱበት ክብደት ይመለሳሉ፤ ከዚያ በኋላ በቀን በአማካይ 28 ግራም ገደማ ይጨምራሉ።
- ካጠቡ በኋላ ጡቶችዎ የላሉ ወይም የለሰለሱ ሆነው ይሰማዎታል።
ሕፃኑ እያደገ ሲሄድ የሚያስፈልገው የወተት መጠን ይለዋወጣል፤ ሰውነትዎም ከእነዚህ ለውጦች ጋር ራሱን ያስማማል። ሕፃኑ በፈጣን ዕድገት ወቅት ላይ ሲሆን፣ በየተወሰነ ጊዜ ወይም ለረጅም ሰዓታት መጥባት ሊፈልግ ይችላል። በዚህ ጊዜም ቢሆን ሰውነትዎ ተጨማሪ ወተት ያመርታል።
ሕፃኑ ርቦት ሊሆን እንደሚችል የሚያሳዩ ምልክቶች፦
- በንቃት መንቀሳቀስ።
- ጡትዎን ለመፈለግ ራሱን ማዞር ወይም ወደ ጡቱ መጠጋት።
- እጆቹን መጥባት፣ ከንፈሩን መምጠጥ ወይም ምላሱን ማውጣት።
- እጆቹን በቡጢ ጨብጦ ወደ አፉ መውሰድ ወይም ጣቶቹን መጥባት (ነገር ግን ከጨቅላነት ዕድሜ በኋላ ይህ ምልክት የረሃብ ሳይሆን የጉጉት/የመፈለግ ምልክት ሊሆን ይችላል)።
ሕፃኑ ጠግቦ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳዩ ምልክቶች፦
- ጡቱን መልቀቅ።
- ዘና ያለ መምሰል።
- ጨብጦት የነበረውን እጅ መዘርጋት።
- ፊቱን ከጡትዎ ማዞር (ነገር ግን ከጨቅላነት ዕድሜ በኋላ ይህ ምልክት ትኩረቱ በሌላ ነገር መሳቡን ሊያሳይ ይችላል)።
ጡት በማጥባት ወቅት የትኞቹን ምግቦች፣ መጠጦች ወይም ንጥረ ነገሮች ማስወገድ ይኖርብኛል?
ልክ እንደ እርግዝና ወቅት ሁሉ፣ ጡት በሚያጠቡበት ጊዜም ለሚመገቡት እና ለሚጠጡት ነገር ትኩረት መስጠት ይኖርብዎታል። ከእርግዝና ጊዜ ጋር ሲነፃፀር በጡት ማጥባት ወቅት የሚጣሉ ክልከላዎች ያነሱ ቢሆኑም፣ በልክ ሊወሰዱ ወይም ሊወገዱ የሚገቡ ነገሮች አሉ፦
- ካፌይንን (Caffeine) ይቀንሱ፦ የተወሰነ መጠን ያለው ካፌይን መውሰድ ችግር የለውም፤ ነገር ግን በቀን ከ 300 ሚሊግራም (mg) መበለጥ የለበትም። ይህም በግምት ሁለት ወይም 3 ሲኒ ቡና ማለት ነው። ሻይ (በአንድ ኩባያ 37 ሚሊግራም ገደማ)፣ ለስላሳ መጠጦች (ከ23-83 ሚሊግራም) እና ቸኮሌቶችንም መቁጠርዎን አይዘንጉ።
- አልኮልን ይቀንሱ፦ ጡት በማጥባት ወቅት በቀን እስከ አንድ መደበኛ የአልኮል መጠጥ (standard drink) መጠጣት የሚታወቅ የጤና ጉዳት የለውም። ነገር ግን ከመጥባትዎ ቢያንስ ሁለት ሰዓት በፊት መጠጣት ይኖርብዎታል። ይህም አልኮሉ ከሰውነትዎ ውስጥ እንዲወገድ ጊዜ ይሰጠዋል።
- ከፍተኛ ሜርኩሪ (Mercury) ያላቸውን ዓሦች ያስወግዱ፦ በሚመገቡት ዓሳ ውስጥ የሚገኝ ሜርኩሪ በጡት ወተት በኩል ወደ ሕፃኑ ሊተላለፍ ይችላል። ይህም የሕፃኑን አእምሮ እና የነርቭ ሥርዓት ሊጎዳ ይችላል።
- ኒኮቲን (Nicotine) ያስወግዱ፦ ሲጋራ ማጨስ ወይም "ቬፒንግ" (vaping) የጡት ወተትዎን ጥራት የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ የወተት ምርትዎ እንዲያንስ ያደርጋል። በተጨማሪም የሲጋራ ጭስ መተንፈስ ለሕፃኑ አለርጂ፣ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን እና ለድንገተኛ የሕፃናት ሞት የመጋለጥ እድልን ይጨምራል።
- አንዳንድ መድኃኒቶችን ያስወግዱ፦ አብዛኛዎቹ የተለመዱ መድኃኒቶች ጡት በማጥባት ወቅት መውሰድ ደህንነቱ የተጠበቀ ነው። ነገር ግን አንዳንዶቹ ሕፃኑን ሊጎዱ ወይም የወተት ምርትን ሊቀንሱ ይችላሉ። ማንኛውንም መድኃኒት ወይም ተጨማሪ ሰፕሊመንት (supplements) ከመውሰድዎ በፊት ሁልጊዜ ሐኪምዎን መጠየቅ ጥሩ ነው።




