የእርግዝና ምርመራ (Pregnancy Test)

Elsabet Azezew
Jul 4, 2026
undefined

                                        የእርግዝና ምርመራ (Pregnancy Test) 

የእርግዝና ምርመራ ነፍሰ ጡር መሆንዎን ወይም አለመሆንዎን ለማወቅ የሚረዳ ቀላልና አስተማማኝ መንገድ ነው። ይህ ምርመራ የሚከናወነው ሂውማን ቾሪዮኒክ ጎናዶትሮፒን (hCG) የተባለውን የእርግዝና ሆርሞን በሰውነት ውስጥ በመለካት ሲሆን፣ የሚከተሉት መሠረታዊ ባሕርያት አሉት፦

  • ይህ ሆርሞን በሰውነትዎ ውስጥ መመረት የሚጀምረው የዳበረው እንቁላል በማህፀን ግድግዳ ላይ ከተጣበቀ በኋላ ነው (ይህም በአብዛኛው ፅንሱ ከተፈጠረ ከ6 እስከ 10 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ይከሰታል)።
  • በምርመራው ወቅት የhCG ሆርሞን ከተገኘ የምርመራው ውጤት አዎንታዊ (ፖዘቲቭ) የሚሆን ሲሆን፣ ይህም እርግዝና መኖሩን ያረጋግጣል።
  • በሰውነት ውስጥ የሆርሞኑ መኖር ካልተገኘ ደግሞ ውጤቱ አሉታዊ (ኔጋቲቭ) ይሆናል።

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ምርመራውን በጣም ቀድመው ካደረጉት በሰውነትዎ ውስጥ ያለው የhCG ሆርሞን መጠን ለምርመራ መሣሪያው ገና በቂ ደረጃ ላይ ላይደርስ ይችላል። በዚህም ምክንያት እርጉዝ ሆነው ሳለ ውጤቱ በስህተት "የሐሰት አሉታዊ" (False-negative) ሊሆን ስለሚችል የወር አበባዎ ከቀረ ከጥቂት ቀናት በኋላ ምርመራውን በድጋሚ ማድረግ ይመረጣል።

                    የእርግዝና ምርመራ ዓይነቶች

ሁለት ዋና ዋና የእርግዝና ምርመራ ዓይነቶች አሉ፤ እነሱም የሽንት ምርመራ እና የደም ምርመራ ናቸው። ሁለቱም የhCG ሆርሞንን የሚለዩ ቢሆንም አሰራራቸው እና እርግዝናን ቀድሞ የመለየት አቅማቸው ግን ይለያያል።

የሽንት እርግዝና ምርመራ

የሽንት ምርመራ በጣም የተለመደው የእርግዝና ምርመራ ዓይነት ሲሆን በቤት ውስጥም ሆነ  በጤና ተቋም ሊከናወን ይችላል ። በቤት ውስጥ የሚደረጉ የራስ መመርመሪያ ቴስቶች (Pregnancy Self-Tests) በስፋት የሚገኙና ለመጠቀም እጅግ ቀላል ናቸው። መመሪያውን ተከትሎ በትክክል ጥቅም ላይ ሲውሉም እስከ 99% አስተማማኝ ውጤት ይሰጣሉ። 

ምንም እንኳን ብዙዎቹ የቤት ውስጥ መመርመሪያዎች ፅንሱ ከተፈጠረ ከ10 ቀናት በኋላ የhCG ሆርሞንን መለየት ቢችሉም ይበልጥ ፍጹምና ትክክለኛ ውጤት ለማግኘት ግን የወር አበባዎ መምጣት ከነበረበት ቀን በኋላ ምርመራውን ቢያደርጉ ይመረጣል። 

በቤት ውስጥ የሚደረግን የእርግዝና ምርመራ ትክክለኛነት ለመጨመር የሚከተሉትን ያድርጉ፦

  • ምርመራውን ከማድረግዎ በፊት የወር አበባዎ እስኪቀር ድረስ ይታገሱ
  • የhCG ሆርሞን በከፍተኛ መጠን ተከማችቶ የሚገኘው የጠዋት የመጀመሪያ ሽንት ላይ ስለሆነ ለምርመራው የጠዋት ሽንትን ቢጠቀሙ ውጤቱን ይበልጥ አስተማማኝ ያደርግሎታል። 
  • ሽንትዎን ሊያቀጥነው (ሆርሞኑን ሊበርዘው) ስለሚችል ምርመራውን ከማድረግዎ በፊት ብዙ ፈሳሽ ከመጠጣት ይቆጠቡ።
  • የመመርመሪያውን የአገልግሎት ማብቂያ ቀን (Expiration date) አስቀድመው ያረጋግጡ፤ እንዲሁም በካርቶኑ የተቀመጡትን መመሪያዎች በጥንቃቄ ይከተሉ። 
  • የhCG ሆርሞን የያዙ የመካንነት ሕክምና መድኃኒቶችን የሚወስዱ ከሆነ ፤ እነዚህ መድኃኒቶች በእርግዝና ምርመራ ውጤትዎ ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ (ውጤቱን ሊያዛቡ) እንደሚችሉ ይገንዘቡ ።

የደም እርግዝና ምርመራ

የደም እርግዝና ምርመራ በጤና ባለሙያ የሚከናወን ሲሆን ለምርመራውም የደም ናሙና ያስፈልጋል። ይህ ምርመራ በአንጻራዊነት ዋጋው ውድ በመሆኑ በብዛት ጥቅም ላይ ባይውልም ከሽንት ምርመራ ይልቅ ግን እርግዝናን አስቀድሞ ለይቶ የማወቅ አቅሙ እጅግ ከፍተኛ ነው ። በዚህም ምክንያት ፅንሱ ከተፈጠረ ከ7 እስከ 10 ቀናት ባለው አጭር ጊዜ ውስጥ እርግዝና መኖሩን ማረጋገጥ ይችላል።

ከሽንት ምርመራ በተለየ መልኩም የደም እርግዝና ምርመራ የሚከተሉት ጥቅሞች አሉት፦

  • በደም ውስጥ የሚገኘውን የhCG ሆርሞን ትክክለኛ መጠን (Quantitative) በትክክል መለካት ይችላል።
  • የጤና ባለሙያዎች የእርግዝናውን ጤናማነት በቅርብ ለመከታተልና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ውስብስብ ችግሮችን አስቀድሞ ለመገምገም ይረዳቸዋል።
  • አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም እርግዝናውን በሕክምና ለመደገፍና ተገቢውን ውሳኔ በጊዜ ለመውሰድ ያስችላቸዋል።

ከእነዚህም ምርመራዎች በተጨማሪ በአንዳንድ ሁኔታዎች የጤና ባለሙያው እርግዝናውን ይበልጥ ለማረጋገጥ እና የፅንሱን ዕድገት ለመገምገም የአልትራሳውንድ (Ultrasound) ምርመራን ሊጠቀም ይችላል።

                 የእርግዝና ምርመራ ማድረግ ያለብዎት መቼ ነው?

ሰዎች በተለያዩ ሁኔታዎችና ምክንያቶች የእርግዝና ምርመራ ሊያደርጉ ይችላሉ። ከእነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው ፦

  • የወር አበባ በሚቀርበት ወይም በሚዘገይበት ጊዜ
  • የእርግዝና ምልክቶች በሰውነት ላይ መታየት ሲጀምሩ
  • ጥቅም ላይ የዋለው የወሊድ መከላከያ ዘዴ ሳይሠራ ቀርቷል የሚል ሥጋት ሲኖር 
  • የተወሰኑ ጠንከር ያሉ መድኃኒቶችን ከመውሰድ ወይም የሕክምና ሂደቶችን ከመጀመር በፊት እርግዝና አለመኖሩን አስቀድሞ ለማረጋገጥ 

እዚህ ላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ፤ አንዳንድ መመርመሪያዎች የወር አበባ ከመቅረቱ በፊት እርግዝናን ለመለየት  ቢችሉም፣ ይበልጥ ትክክለኛና አስተማማኝ ውጤት ለማግኘት ግን የወር አበባዎ መምጣት የነበረበት ቀን ካለፈ በኋላ ምርመራውን ማድረግ ይመረጣል።

                በቤት ውስጥ የሚደረግ የእርግዝና ምርመራ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

በቤት ውስጥ የሚደረጉ የራስ መመርመሪያ ቴስቶች (Pregnancy Self-Tests) የሚሰጧቸው ዋነኛ ጥቅሞች የሚከተሉት ናቸው፦ 

  • ዋጋቸው አነስተኛ እና ተመጣጣኝ ከመሆኑም በላይ በማንኛውም ፋርማሲ ውስጥ በስፋት በቀላሉ ይገኛሉ
  • መሪያዎቻቸው እጅግ ግልጽ በመሆናቸው ማንኛውም ሰው ያለ ባለሙያ እገዛ በቤቱ ሊጠቀምባቸው ይችላል 
  • ረጅም ሰዓት ሳይጠብቁ በአጭር ጊዜ ውስጥ (በአብዛኛው ከ3 እስከ 5 ደቂቃዎች ባለው ጊዜ) ፈጣን ምላሽ ይሰጣሉ 
  • በትክክለኛው ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውሉ ውጤታቸው ትክክለኛ እና አስተማማኝ ነው 

                የምርመራ ውጤትዎን መረዳት

አብዛኞቹ የቤት ውስጥ የእርግዝና መመርመሪያዎች በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ውጤት ያሳያሉ። ይሁን እንጂ ውጤቱን በትክክለኛው መንገድ ለመተርጎም የሚከተሉትን ወሳኝ ነጥቦች ልብ ማለት ያስፈልጋል፦

  • ውጤቱን በመመሪያው ላይ በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ ብቻ ማንበብዎን ያረጋግጡ። ከተባለው ሰዓት አሳልፎ ማየት “የትነት መስመር” (Evaporation line) እንዲፈጠር ስለሚያደርግ፣ እርግዝና ሳይኖር በስህተት እንደ አዎንታዊ (ፖዘቲቭ) ውጤት ሊቆጠር ይችላል።
  • በመመርመሪያው ላይ የሚታይ ማንኛውም ደብዛዛ መስመርም ቢሆን እርግዝና መኖሩን ሊያመለክት ይችላል። ይህም በአብዛኛው የሚከሰተው ምርመራውን በጣም ቀድመው (የሆርሞኑ መጠን ገና አነስተኛ በሆነበት ጊዜ) ሲያደርጉት ነው።
  • የምርመራ ውጤትዎ ግልጽ ካልሆነ፣ የእርግዝና ምልክቶች እያሉዎትም ውጤቱ አሉታዊ (ኔጋቲቭ) ከሆነ ወይም ውጤቱን ለማንበብ ከተቸገሩ ከ48 ሰዓታት በኋላ ምርመራውን ድጋሚ ይስሩ ወይም ደግሞ ለተሻለ ውሳኔ ሐኪምዎን ያማክሩ።

               የእርግዝና መመርመሪያዎች የተሳሳተ ውጤት ሊያሳዩ ይችላሉ?

በቤት ውስጥ የሚደረጉ የእርግዝና መመርመሪያዎች ብዙ ጊዜ ትክክለኛ ውጤት የማሳየት አቅማቸው ከፍተኛ ቢሆንም አልፎ አልፎ ግን የተሳሳቱ ውጤቶች ሊያሳዩ ይችላሉ።ከእነዚህም መካከል በጣም የተለመደው ስህተት “የሐሰት ኔጋቲቭ” (false-negative) ሲሆን “የሐሰት አዎንታዊ” (False-positive) ውጤት ግን እጅግ በጣም አልፎ አልፎ የሚከሰት ነው። 

የሐሰት ኔጋቲቭ (False-Negative) ውጤት ምንድን ነው? 

የሐሰት ኔጋቲቭ ማለት እርጉዝ ሆነው ሳለ መመርመሪያው "እርጉዝ አይደሉም" የሚል ውጤት ሲያሳይ ነው። ይህ በሚከተሉት ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል፦

  • ሰውነትዎ በቂ የhCG ሆርሞን ማመንጨት ከመጀመሩ በፊት ምርመራው ከተደረገ
  • ሽንትዎ በጣም የቀጠነ ከሆነ (ይህ ብዙ ጊዜ የሚከሰተው ከመመርመርዎ በፊት ከፍተኛ መጠን ያለው ፈሳሽ ሲጠጡ ነው)
  • ውጤቱን ለማንበብ በመመሪያው ላይ የተጠቀሰውን ትክክለኛ ደቂቃ ሳይጠብቁ ቀድመው ካዩት 
  •  እንደ ማረጋጊያ (tranquilizers) ወይም የሚጥል በሽታያ መድኃኒቶች (anticonvulsants) ያሉ አንዳንድ መድኃኒቶችን የሚወስዱ ከሆነ እና በውጤቱ ላይ ጣልቃ ሲገቡ

የሐሰት ፖዘቲቭ (False-Positive) ውጤት ምንድን ነው? 

የሐሰት ፖዘቲቭ ማለት እርጉዝ ሳይሆኑ ሳለ መመርመሪያው "እርጉዝ ኖት" የሚል ውጤት ሲያሳይ ነው። ይህ ሁኔታ በጣም አልፎ አልፎ የሚከሰት ቢሆንም በሚከተሉት ምክንያቶች ሊፈጠር ይችላል፦

  • የኬሚካል እርግዝና (Chemical pregnancy) ፦ ፅንሱ በማህፀን ግድግዳ ላይ ከተጣበቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ እርግዝናው በራሱ የሚቋረጥበት አጋጣሚ ሲኖር 
  • ከማሕፀን ውጭ የሆነ እርግዝና (Ectopic pregnancy) ሲኖር
  • የማረጥ ዕድሜ (Menopause) ላይ ሲደረስ
  • አንዳንድ የእንቁልጢ (Ovarian) ችግሮች ለምሳሌ የእንቁልጢ ውሃ መቋጠር (Ovarian cysts) ሲኖር

በእርግዝና መመርመሪያው ላይ አዎንታዊ (ፖዘቲቭ) ውጤት አግኝተው፣ ነገር ግን ያልተለመዱ የሕመም ምልክቶች (እንደ ከፍተኛ የሆድ ወይም የዳሌ ሕመም) ከተሰሙዎት ወይም ውጤቱ የተሳሳተ ነው የሚል ሥጋት ካለዎት ሐኪምዎን ያማክሩ። ሐኪምዎ እርግዝናውን በእርግጠኝነት ለማረጋገጥ ምርመራውን ሊደግም፣ የደም ምርመራ ወይም የአልትራሳውንድ ምርመራ ሊያደርጉልዎ ይችላል።

Comments (0)