እርጉዝ ነዎት? ሆድዎስ ያሳክክዎታል?

Elsabet Azezew
Jul 19, 2026
undefined

                                                እርጉዝ ነዎት? ሆድዎስ ያሳክክዎታል? 

ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያረግዙ፣ እንደ ማቅለሽለሽ፣ የእግር ማበጥ፣ የምግብ ፍላጎት መለዋወጥና የቃር ስሜት ያሉ የተለመዱ የእርግዝና ምልክቶች ሊያጋጥሙዎት እንደሚችሉ አስበው ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ጨርሶ ሳያስቡት ሊመጣ እና ግራ ሊያጋብዎት የሚችለው ምልክት የሆድ ወይም የእንብርት አካባቢ ማሳከክ ነው። 

በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የቆዳ ማሳከክ (Pruritus) ከሚያስቡት በላይ እጅግ የተለመደ ክስተት ነው። ይህ አብዛኛውን ጊዜ በሰውነትዎ ውስጥ በሚፈጠሩ ተፈጥሯዊ ለውጦች ምክንያት የሚመጣ ቢሆንም በአንዳንድ ሁኔታዎች ግን የሕክምና ክትትል የሚሻ የሌላ የጤና ችግር ምልክት ሊሆንም ይችላል። 

በዚህ ጽሑፍ የሆድ ወይም የእንብርት አካባቢ ሊያሳክክዎት የሚችልባቸውን ዋና ዋና ምክንያቶች እና በዚህ ወቅት እፎይታ ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብዎት በዝርዝር እንመለከታለን። 

                   በእርግዝና ወቅት የሆድ ማሳከክን የሚያስከትሉ ዋና ዋና መንስኤዎች

በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የሆድ ማሳከክ በተለመዱ (ፊዚዮሎጂያዊ) ለውጦች ወይም አልፎ አልፎ በሚከሰቱና የሕክምና ክትትል በሚሹ የጤና እክሎች ምክንያት ሊመጣ ይችላል። 

       የተለመዱና መደበኛ መንስኤዎች  

  • የቆዳ መለጠጥ

ልጅዎ እያደገ ሲሄድ፣ እየሰፋ የመጣውን ማህፀንዎን ለማስተናገድ ሲል በሆድዎ አካባቢ ያለው ቆዳ ይለጠጣል። ይህ መለጠጥ በተለይ በሆድና በእንብርት አካባቢ የቆዳ መወጠርን፣ መድረቅንና ማሳከክን ያስከትላል። ከዚህም በተጨማሪ ቆዳ ላይ የመለጠጥ ምልክቶች (Stretch marks) እንዲፈጠሩ ሊያደርግ የሚችል ሲሆን ይህም ማሳከኩን ይበልጥ ያባብሰዋል። 

  • የቆዳ መድረቅ

በእርግዝና ወቅት የሚከሰቱ የሆርሞን ለውጦች የቆዳን ተፈጥሯዊ እርጥበት ሊቀንሱት ይችላሉ። ይህም ቆዳ እንዲደርቅ፣ እንዲሰነጣጠቅ እና ማሳከክ እንዲጀምር ያደርጋል። ይህ ሁኔታ ከእርግዝና ማሳከክ ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ነው። 

      ብዙም ያልተለመዱ ነገር ግን ትኩረት የሚሹ መንስኤዎች 

  • ፒ.ዩ.ፒ.ፒ.ፒ (PUPPP)

ይህ ምንም አይነት ጉዳት የሌለው የእርግዝና ሽፍታ ሲሆን ብዙውን ጊዜ በሦስተኛው የእርግዝና ምዕራፍ (በመጨረሻዎቹ ወራት) ላይ ይከሰታል። ይህ እክል በተለይ በመጀመሪያ እርግዝና ላይ የሚስተዋል ሲሆን በሆድ ላይ ጀምረው ወደ ጭን እና መቀመጫ በሚሰራጩ ትናንሽ፣ የሚያሳክኩ ቀይ እብጠቶች ወይም እንደ አለርጂ ያሉ ሽፍታዎች ይገለጻል። ማሳከኩ በጣም ከባድ ሊሆን ቢችልም፣ ከወሊድ በኋላ ወዲያውኑ ይጠፋል። በቀዝቃዛ ውሃ የተነከረ ፎጣ (Cool compresses) በማድረግ፣ በአጃ ውሃ በመታጠብና ሐኪምዎ የሚያዙልዎትን መድኃኒቶች በመጠቀም ምልክቶቹን ማስታገስ ይቻላል። 

  • ፔምፊጎይድ ጄስታሺዮኒስ (Pemphigoid Gestationis)

ይህ አልፎ አልፎ የሚከሰትና በሰውነት የበሽታ መከላከል ሥርዓት መዛባት (Autoimmune) ምክንያት የሚመጣ የቆዳ በሽታ ነው። ፔምፊጎይድ ጄስታሺዮኒስ ከፍተኛ ማሳከክ ካለው ሽፍታ በተጨማሪ ውሃ የቋጠሩ ቁስሎችን (Blisters) ያስከትላል። 

ይህም እክል ብዙውን ጊዜ በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው የእርግዝና ምዕራፍ የሚከሰት ሲሆን ምልክቶቹን ለመቆጣጠር የሕክምና ምርመራ እና ህክምና ያስፈልጎታል።

  • የእርግዝና የጉበት ኮሌስታሲስ (Intrahepatic Cholestasis of Pregnancy - ICP)

ይህ ሁኔታ በተፈጥሯዊ መንገድ መፍሰስ ያለበት የሐሞት ፈሳሽ (Bile) በጉበት ውስጥ ሲከማች እና ወደ ደም ሲቀላቀል የሚከሰት ነው።  ይህ ችግር ከሌሎች የእርግዝና ማሳከክ መንስኤዎች በተለየ መልኩ ያለምንም ሽፍታ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ማሳከክን ያስከትላል። ። አብዛኛውን ጊዜ ማሳከኩ ወደ ሆድ ከመሰራጨቱ በፊት በእጅ መዳፍና በእግር ጫማ ላይ ይጀምራል። 

የእርግዝና የጉበት ኮሌስታሲስ (ICP) ሕፃኑ ያለጊዜው እንዲወለድ ወይም በማህፀን ውስጥ የመሞት (Stillbirth) አደጋን ሊጨምር ስለሚችል አስቸኳይ የሕክምና ክትትል ያስፈልገዋል። ከከባድ ማሳከክ በተጨማሪ የሚከተሉት ምልክቶች ከታዩ ፈጥነው ወደ ሕክምና ተቋም ይሂዱ፦ 

              - የቆዳ ወይም የዓይንቢጫ መሆን (Jaundice/ወፍ በሽታ)

              - የሽንት ቀለም በጣም መጥቆር እና 

              - የሰገራ ቀለም ወደ ነጭ/አመድማ መለወጥ

                  በእርግዝና ወቅት የሆድ ማሳከክን ለማስታገስ የሚረዱ የቤት ውስጥ መፍትሔዎች

በእርግዝና ወቅት የሚኖረውን የሆድ ማሳከክ ለማስታገስ እና ምቾት እንዲሰማዎት ለማድረግ የሚረዱ ቀላል የቤት ውስጥ መፍትሔዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል

  • የአጃ ገንዳ መታጠቢያ (Oatmeal Bath)

አጃ የቆዳ መቆጣትን የሚያስታግሱና ማሳከክን የሚቀንሱ ተፈጥሯዊ ባህሪያት አሉት። 

1 ኩባያ አጃ ለብ ባለ ውሃ በተሞላ ገንዳ ወይም መዘፍዘፊያ ውስጥ በመጨመር በቀን አንድ ጊዜ ለ15 እስከ 20 ይዘፍዘፉ።

  • የሽንብራ ዱቄት (Gram Flour/Besan Paste)

ይህ ውህድ ማሳከክን ለማስታገስና የደረቀ ቆዳን ለማለስለስ የሚረዳ ባህላዊ ዘዴ ነው። 

1 የሾርባ ማንኪያ የሽንብራ ዱቄት ከጥቂት እርጎ ጋር በመቀላቀል ቀጠን ያለ ውህድ ያዘጋጁ። ከዚያም የሚያሳክኮት ቦታ ላይ በመቀባት ከደረቀ በኋላ (ከ30 ደቂቃ በኋላ) ይታጠቡት። ይህንን በቀን አንድ ጊዜ ይጠቀሙ።

  • የኮኮናት ዘይት (Coconut Oil)

የኮኮናት ዘይት ላውሪክ አሲድ (lauric acid) የተባለውን ተፈጥሯዊ ንጥረ ነገር በውስጡ በመያዙ ቆዳን በጥልቀት የማለስለስ፣ እርጥበት የመስጠትና ድርቀትን የመከላከል ከፍተኛ አቅም አለው። 

የኮኮናት ዘይቱን በሚያሳክክዎት ቦታ ላይ በመቀባት ከ30 እስከ 40 ደቂቃ ወይም ለአንድ ሌሊት አቆይተው ይታጠቡት። ይህን በቀን አንድ ጊዜ ያድርጉ።  

  • የሬት ጄል (Aloe Vera Gel)

ሬት ቆዳን የማቀዝቀዝ፣ የማለስለስ እና መቆጣትን የመከላከል አስደናቂ ተፈጥሯዊ ባህሪ አለው። 

የሬት ጄሉን የሚያሳክኮት ቦታ ተቀብተው ለ30 ደቂቃ ካቆዩት በኋላ ይታጠቡት። ለተሻለ ውጤት በሳምንት ከ2 እስከ 3 ጊዜ ይጠቀሙ። 

  • እንደ ሮዝ ጄራንየም ያሉ የእፅዋት ዘይቶች (Essential Oils)

እንደ ሮዝ ጄራንየም ያሉ የእፅዋት ዘይቶች በትክክል ጥቅም ላይ ሲውሉ ማሳከክን እና የቆዳ መቅላትን ለማስታገስ ይረዳሉ። ይሁን እንጂ ሁሉም የዕፅዋት ዘይቶች በእርግዝና ወቅት ደኅንነታቸው የተጠበቀ ባለመሆኑ (ለምሳሌ፦ ጁኒፐር/Juniper ማህፀንን የማኮማተር ሥጋት ስላለው) ከመጠቀምዎ በፊት የግድ ሐኪምዎን ማማከር ይኖርብዎታል። 

በሐኪም ከተፈቀደልዎም 10 ጠብታ የዕፅዋት ዘይት ከ2 የሾርባ ማንኪያ የኮኮናት ዘይት ጋር በደንብ አዋህደው ይቀቡት፤ ከዚያም ለአንድ ሰዓት ያህል አቆይተው ይታጠቡት። ማሳከኩ ይበልጥ እንዲቀንስልዎ ይህንን በቀን ሁለት ጊዜ ማድረግ ይችላሉ። 

  • የተበረዘ የሎሚ ጭማቂ (Diluted Lemon Juice) 

ሎሚ ተሕዋስያንን የመከላከልና የቆዳን ተፈጥሯዊ የፒኤች (pH) ሚዛን የመጠበቅ ባሕርይ ስላለው የቆዳ መቆጣትን ለማስታገስ በእጅጉ ይረዳል። 

1 የሾርባ ማንኪያ የሎሚ ጭማቂ ከሩብ ኩባያ ውሃ ጋር በመቀላቀል በጥጥ ቀስ አድርገው ይቀቡት።  ከዚያም ከ20 እስከ 30 ደቂቃ በኋላ ይታጠቡት ። ቆዳን ሊያቃጥል ስለሚችል ይህን የተላጠ፣ የቆሰለ ወይም በጣም ስስ ቆዳ ላይ በፍጹም አይጠቀሙት። 

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር እነዚህ የቤት ውስጥ ሕክምናዎች የሚያገለግሉት መጠነኛ ማሳከክን ለማስታገስ ብቻ ነው። ነገር ግን ማሳከኩ በጣም ከባድ ከሆነ፣ በእጅዎ መዳፍና በእግርዎ ጫማ ላይ ከበረታ ወይም ከሽፍታና ከሌሎች ምልክቶች ጋር አብሮ ከመጣ ሐኪምዎን ማማከር ይኖርብዎታል። 

                 የሆድ ማሳከክን ለማስታገስ የሚረዱ ተጨማሪ መፍትሔዎች 

ከላይ ከተጠቀሱት ዋና ዋና የቤት ውስጥ መፍትሔዎች በተጨማሪ የቆዳዎን ምቾት ለመጠበቅና ማሳከኩን በዘላቂነት ለመከላከል የሚከተሉትን የዕለት ተዕለት ልምዶች መተግበር ይችላሉ 

      የውጭ የቆዳ እንክብካቤ (External Skin Care) 

  • በየቀኑ ቆዳዎ እርጥበት እንዲኖረው ያድርጉ (Moisturize Daily)

እርጥበትን በቆዳዎ ውስጥ ለማስቀረት እና የቆዳ መድረቅን ለመከላከል በተለይ ከታጠቡ በኋላ ወዲያውኑ ወፍራምና መዓዛ የሌለው (Fragrance-free) የቆዳ ማለስለሻ ወይም በእርግዝና ወቅት ደኅንነቱ የተረጋገጠ ሎሽን በሆድዎ ላይ ይቀቡ። 

  • ቀዝቃዛ ፎጣ ማድረግ (Cool Compresses) 

የቆዳ መቆጣትን ለመቀነስና ፈጣን እፎይታ ለማግኘት፣ ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ የተነከረ ፎጣ ወይም በፎጣ የተጠቀለለ በረዶ የሚያሳክክዎት ቦታ ላይ ለጥቂት ደቂቃዎች ይያዙት። 

  • ካላሚን ሎሽን (Calamine Lotion) ይጠቀሙ

ካላሚን ሎሽን ማሳከክን ለመቀነስና የተቆጣ ቆዳን ለማስታገስ እጅግ ፍቱን መፍትሔ ነው። ሎሽኑን በስሱ ይቀቡ። ማሳከኩን ለማስታገስ ይህን በቀን ሁለት ጊዜ ያድርጉ።

  • ለብ ባለ ውሃ ይታጠቡ (Take Lukewarm Showers)

ቆዳን ሊያደርቅ እና ማሳከክን ሊያባብስ ስለሚችሉ በሙቅ ውሃ ከመታጠብ ይቆጠቡ። ይልቁንስ ለስላሳና መዓዛ ከሌለው ሳሙና ጋር ለብ ያለ ውሃ ይጠቀሙ። ከታጠቡ በኋላም ቆዳዎን በፎጣ በቀስታ ያድርቁት። 

     የአኗኗር ዘይቤ እና የአመጋገብ ለውጥ (Diet & Lifestyle) 

  • በቂ ውሃ ይጠጡ (Stay Hydrated)

በቂ ፈሳሽ መጠጣት ቆዳዎ ከውስጥ ጀምሮ እርጥበት እንዲኖረው ስለሚያደርግ የቆዳ ማሳከክን በእጅጉ ይቀንሳል።  

  • ለቆዳ ጤናማ ምግቦችን ይመገቡ (Eat Skin-Healthy Foods)

የቆዳዎን የመለጠጥ አቅምና ጤና ለመደገፍ የሚከተሉትን ምግቦች በአመጋገብዎ ውስጥ ያካቱ፦ 

          - በኦሜጋ-3 የበለጸጉ ምግቦች፦ ሳልመን፣ ሰርዲን፣ ተልባ እና ዋልነት (Walnuts)

          - በቫይታሚን ኢ የበለጸጉ ምግቦች፦ ለውዝ፣ የሱፍ ፍሬ፣ ስፒናች እና አቮካዶ

          - አንቲኦክሲዳንት ያላቸው ምግቦች ፦ እንጆሪ (Berries)፣ አረንጓዴ ቅጠላቅጠሎች፣ ካሮት እና ወይን                                                                                                                

  • ማሳከክን የሚያባብሱ ምግቦችን ያስወግዱ (Avoid Common Triggers)

ቃሪያና ቅመም የበዛባቸው ምግቦች፣ እንዲሁም ካፌይንና ስኳር የበዛባቸው መጠጦች በሰውነት ውስጥ የደም ዝውውርን በመጨመር ማሳከክዎን ሊያባብሱ ስለሚችሉ አጠቃቀምዎን ለመቀነስ ይሞክሩ። 

                ሐኪምዎን መቼ ማማከር ይኖርብዎታል? 

በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የሆድ ማሳከክ አብዛኛውን ጊዜ ጉዳት የሌለውና የማህፀንዎ መጠን በመጨመሩ (በቆዳ መለጠጥ) ምክንያት የሚመጣ የተፈጥሮ ክስተት ነው። ይሁን እንጂ ማሳከኩ እጅግ ከፍተኛ እና በቤት ውስጥ መፍትሔዎች የማይሻሻል ከሆነ ወይም ከሌሎች ምልክቶች ጋር አብሮ ከመጣ ከበስተጀርባው ሌላ የጤና እክል አለመኖሩን ለማረጋገጥ የግድ ሐኪምዎን ማማከር ያስፈልጋል። 

ማሳከኩ በጣም ከባድና እንቅልፍ የሚነሳዎት መሆኑን ሐኪምዎ ካረጋገጠ ምልክቶቹን በፍጥነት ለማስታገስ በእርግዝና ወቅት ለመጠቀም ደኅንነታቸው የተጠበቀና ቆዳ ላይ የሚቀቡ እንደ ኮርቲኮስቴሮይድ (Topical Corticosteroid) ወይም አንቲሂስታሚን (Antihistamine) ያሉ መድኃኒቶችን ሊያዙልዎት ይችላል። 

Comments (0)