በሽታ የመከላከል ስርዓትን በተፈጥሮ እንዴት ማሳደግ ይቻላል? (How To Boost Your Immune System Naturally)
ሰውነትን ከበሽታ፣ ከቫይረሶች እና ከሌሎች ህመሞች ለመጠበቅ ጠንካራ የበሽታ መከላከያ ስርዓት አስፈላጊ ነው። በሽታን ለማስወገድ ምንም አይነት ዋስትና ያለው መንገድ ባይኖርም፣ አንዳንድ የአኗኗር ዘይቤዎች የበሽታ መከላከያ አቅሞን ያጠናክራሉ ።የበሽታ መከላከል አቅምን ማሳደግ ቀጣይነት ያለው የሕይወት ዘይቤ እንጂ በአንድ ጀምበር የሚገኝ አቋራጭ መፍትሔ የለውም።
በሽታ የመከላከል ብቃትን ከሚጨመሩ ነገሮች በጥቂቱ፡-
የተመጣጠነ ምግብ ይመገቡ!
የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ፡ ማለት በንጥረ-ምግብ የበለጸጉ ምግቦች ላይ ማትኮር ፍራፍሬ፣ አትክልት፣ ሙሉ እህል እና ጥራጥሬዎች ፣ ፕሮቲን እና ጤናማ ቅባቶችን ያካተተ የተመጣጠነ ምግብ ይመገቡ።
እነዚህ ምግቦች ኢንፍላሜሽንን ለመቀነስ፣ የአንጀትን ጤንነት ለመጠበቅ እና የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅምን ለማጎልበት በሚያስችሉ አንቲኦክሲደንቶች፣ ቫይታሚኖች፣ ሜኔራሎች እና ፋይበር የበለፀጉ ናቸው።
ጤናማ ክብደትን መጠበቅ፡ ከመጠን በላይ መወፈር ወይም ክብደት መቀነስ የሰውነትን በሽታ የመከላከል ስርዓትን ሊጎዳ ይችላል, ስለዚህ በተመጣጠነ አመጋገብ እና መደበኛ የአካል እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት በማድረግ ጤናማ የሰውነት ክብደትን መጠበቅ ያስፈልጋል።
በቂ እንቅልፍ ያግኙ!
እንቅልፍ ሰውነታችን እራሱን ለመጠገን እና ለማደስ እጅግ አስፈላጊ ነው። እንቅልፍ ከሁሉ በላይ ጠንካራው የተፈጥሮ መከላከያ ማሳደጊያ ነው። እንቅልፍ ማጣት የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅምን ሊያዳክም እና ለበሽታ የበለጠ ተጋላጭ ያደርገናል። አዋቂ ሰዎች ማታ ላይ ቢያንስ ለ 7 ሰአታት ያህል ለመተኛት ማቀድ አለባቸው።
በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች ከ8-10 ሰአታት እንዲሁም ትናንሽ ልጆች እና ሕፃናት እስከ 14 ሰዓታት ድረስ እንቅልፍ መተኛት ያስፈልጋቸዋል።የሌሊት እንቅልፍ ለበሽታ መከላከል እና ለማገገም አስፈላጊ ነው። እንቅልፍ ማጣት የበሽታ መቋቋም ምላሽ መቀነስ ሊያስከትል ይችላል። በጥሩ ሁኔታ በሚተኙበት ጊዜ፣ ሰውነትዎ ራሱን ከመጠገኑ ባለፈ ኢንፌክሽኖችን እና በሽታዎችን በብቃት የሚዋጉ ዋና ዋና የበሽታ መከላከል ሕዋሳትን (Immune cells) ያመርታል።
አዘውትረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ!
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የደም ዝውውርን ለማሻሻል፣ የደም ግፊትን ለመቀነስ፣ የጭንቀት መጠንን ለመቀነስ እና ጡንቻዎችን እና አጥንቶችን ለማጠንከር ይረዳል። መደበኛ ቀላል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ማለትም መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ እንደ መራመድ ወይም ብስክሌት መንዳት፣ የደም ዝውውርን በማሻሻል እና የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅምን በማጎልበት የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅምን ይጨምራሉ። ይህም የበሽታ መከላከል ሕዋሳት በሰውነታችን ውስጥ በፍጥነት እንዲዘዋወሩ እና ማንኛውንም የደህንነት ስጋት ወይም ጀርሞች(ባክቴሪያ) ቀድመው አግኝተው እንዲዋጉ እና እንዲያጠፉ ይረዳቸዋል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ኢንፌክሽንን የሚዋጉ የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳትን እና አንቲበዲዎችን እንዲመረቱ ያበረታታል።
በሳምንት ቢያንስ ለ150 ደቂቃዎች ያህል መጠነኛ-ጥንካሬ ያለው ኤሮቢክ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወይም በሳምንት ለ 75 ደቂቃዎች ያህል ጠንካራ ወይም ኃይለኛ ኤሮቢክ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ።
ጭንቀትዎን ይገድቡ!
ጭንቀትና ውጥረት በሽታን የመከላከል ስርዓትን ተግባር የሚቀንሱ እና ብግነትን (ኢንፍላሜሽንን ) የሚጨምሩ ሆርሞኖችን በመልቀቅ በሽታን የመከላከል ስርዓትዎ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል። ጭንቀትን መቆጣጠር፣ እንደ ዮጋ፣ ጥልቅ የአተነፋፈስ ልምምዶች እና የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ መዝናኛዎችን መጠቀም አለብን።
ሥር የሰደደ ጭንቀት ወደ ድብርት፣ ብስጩነት እና ሌሎች የአዕምሮ ጤና ችግሮች በተጨማሪም የበሽታ የመከላከል አቅምን ሊጎዱ ይችላሉ። ጭንቀት የሰውነትን የበሽታ መከላከል አቅም በእጅጉ ያዳክማል። ምክንያቱም ጭንቀት በሰውነት ውስጥ የጭንቀት ሆርሞኖችን በመጨመር ሰውነታችን በሽታን የመዋጋት አቅሙን እንዲያጣ ስለሚያደርግ ነው።
ጭንቀትን ለመቋቋም እንደ ጥሞና፣ ዮጋ፣ የጥልቅ አተነፋፈስ ልምምዶች ወይም ማሳጅ የመሳሰሉ ዘና የሚያደርጉ ዘዴዎችን መሞከር ይችላሉ።
ማጨስ ያቁሙ!
ማጨስ ሳንባዎን ሊጎዳ እና በመተንፈሻ አካላት በሽታዎች የመያዝ እድልን ይጨምራል። እንዲሁም የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳትዎን ተግባር ሊጎዳ እና የአንቲበዲዎችን ውጤታማነት ሊቀንስ ይችላል።
ማጨስ በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰተውን የጉንፋን በሽታ ምልክቶች እና ተጓዳኝ የጤና ችግሮችን ሊያባብስ ይችላል። በተጨማሪም ከአደንዥ እፆች ራስን ማራቅ አደንዛዥ እፆች የበሽታ መከላከያ ሴሎችን ስለሚጎዱ እና የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅምን ስለሚያዳክሙ ከመጠቀም መገደብ በጣም አስፈላጊ ነው።
ብዙ ፈሳሽ ይጠጡ!
ፈሳሾች ከሰውነትዎ ውስጥ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን ለማስወገድ እና የሙከስ ሜምብሬን (Mucous Membrane) እርጥበትን ለመጠበቅ ይረዳሉ።
ይህ ማለትም ንፍጥ ወይም ሙከስ ጀርሞች በአፍንጫዎ እና በአፍዎ ወደ ሰውነትዎ እንዳይገቡ ለመከላከል ይረዳል። በቂ ውኃ መጠጣት በሰውነታችን ውስጥ መርዞችን ለማስወገድ (Detox) እና ንጥረ-ነገሮችን ለማጓጓዝ ስለሚረዳ፣ የበሽታ መከላከል ሥርዓትን ጨምሮ እያንዳንዱ የሰውነት ክፍል ያለ ምንም መስተጓጎል በሰላም እንዲሠራ ያደርጋል።
እርጥበትን ለመጠበቅ ወይም ድርቀትን ለመከላከል ውሃ መጠጣት በጣም ጥሩው ምርጫ ነው። በቂ ውሃ መጠጣት የሰውነትን ተግባር ይጠብቃል። ከውሃ በተጨማሪ ስኳር ያልበዛበት ከዕፅዋት የተቀመመ ሻይ፣ ሾርባዎች፣ ጭማቂዎች ወይም ጁሶችን መጠጣት ይችላሉ።
በምግብ ገበታዎ ውስጥ ፕሮባዮቲኮችን ያካትቱ!
ፕሮባዮቲኮች (Probiotics) በአንጀትዎ ውስጥ የሚኖሩና የማይክሮባዮም ሚዛንን ለመጠበቅ የሚረዱ ጠቃሚ ባክቴሪያዎች ናቸው። እነዚህ አስፈላጊ ባክቴሪያዎች የሰውነትን በሽታ የመከላከል ስርዓትን ለማስተካከል እና ከጎጂ ተህዋሲያን ለመከላከል ይጠቅሙናል።
እንደ:- እርጎ፣ እንጀራ፤ ኪምቺ፣ ሚሶ ወይም ቴምፔ (kefir, sauerkraut, kimchi, miso, or tempeh) ካሉ ፈርመንትድ ምግቦች ፕሮባዮቲኮችን ማግኘት ይችላሉ።
እንዲሁም ከሐኪምዎ ጋር ተመካክረው የፕሮቢዮቲክ ሰፕሊመንቶችን መውሰድ ይችላሉ።
መከላከል ለሚችሏቸው በሽታዎች ክትባት ይውሰዱ!
ክትባቶች ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል እና በሽታ የመከላከል አቅምን ለማጠናከር በጣም ውጤታማ ከሆኑ መንገዶች አንዱ ነው። ክትባቶች የሚሰሩት ሰውነትዎን ለተዳከመ ወይም ንቁ ያልሆነ የጀርም አይነት በማጋለጥ ነው። ይህም አንቲበዲዎችን የሚያመነጭ የበሽታ መቋቋም ምላሽን ያነሳሳል።እነዚህ አንቲበዲዎች ተመሳሳይ ተህዋስያንን ለወደፊቱ እንደገና ካጋጠሙን ሊያውቋቸው እና ሊዋጓቸው ይችላሉ። በዚህም ምክንያት ለእነዚህ ጀርሞች የሚከሰቱ እንፌክሽኖች እንዳይዙን ይረዳናል።
ጥሩ የንጽህና አጠባበቅ ልማዶች ይኑርዎ!
የጀርሞችን እና የኢንፌክሽን ስርጭትን ለመከላከል ንጽህና መጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነው።አዘውትሮ እጅን በሳሙና መታጠብ፣ ንፁህ አካባቢን መጠበቅ እና የንፅህና አጠባበቅ ልማዶችን መለማመድ በሽታ አምጪ ተህዋሲያትን ለመከላከል ይረዳል።
በተለይም ፊትዎን ከመንካትዎ ወይም ምግብ ከመመገብዎ በፊት እጅዎን በሳሙና እና በውሃ ደጋግመው መታጠብ ወይም ከአልኮል የተሰሩ ሳኒታይዘሮችን መጠቀም አለብዎት። በሚያስሉበት ወይም በሚያስነጥሱበት ጊዜ አፍዎን እና አፍንጫዎን በሶፍት ወይም በክርንዎ ይሸፍኑ። ከዚያም የተጠቀሙበትን ሶፍት በትክክል ያስወግዱት። እንዲሁም የተጠቀምናቸውን ዕቃዎችን፣ ኩባያ ወይም የጥርስ ብሩሾች ያሉ የግል መገልገያ ቁሶችን ከሌሎች ጋር ከማጋራት መቆጠብ አለብዎት።
በሽታ የመከላከል አቅምን ሊያሳድጉ የሚችሉ የተፈጥሮ ሰፕሊመንቶችን ይውሰዱ!
በሽታን የመከላከል አቅምን የሚያጎለብቱ አንዳንድ የተፈጥሮ ሰፕሊመንቶች ቪታሚን ሲ፣ ቫይታሚን ዲ፣ ዚንክ፣ ቫይታሚን ኢ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ዝንጅብል፣ እርድ፣ አርጋኖ ዘይት፣ ጂንሲንግ ስር ወይም ሩት እና የእንጉዳይ ተዋጽኦዎች ናቸው።
ይሁን እንጂ ማንኛውንም ተጨማሪ መስተጋብሮች ወይም የጎንዮሽ ጉዳቶችን ለማስወገድ ማንኛውንም አይነት ሰፕሊመንት ከመውሰድዎ በፊት ሁልጊዜ ለሰዉነቶ አስፈላጊ እና ተስማሚ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ከሐኪምዎ ጋር መማከር አለብዎት።
ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ የሰውነትን በሽታ የመከላከል ስርዓትን ለመጠበቅ እና ለማጠናከር, የተሻለ ጤናን እና በሽታዎችን የመቋቋም ቁልፍ ነው ።




