በማረጥ ወቅት ጤናሽን እንዴት መጠበቅ ትችያለሽ?
ማረጥ (Menopause) በሴቶች የሕይወት ዑደት ውስጥ የሚከሰት ተፈጥሯዊ የሰውነት ለውጥ ነው። ማረጥ በአብዛኛው ከ45–55 ዓመት ባለው ዕድሜ መካከል የሚከሰት ሲሆን በዚህ ወቅት የኤስትሮጅን እና ሌሎች ሆርሞኖች መጠን መቀነስ ዋነኛው መንስኤ ነው።
የሰውነት ሙቀት በድንገት መጨመር፣ ሌሊት ላይ ላብ መብዛት፣ የእንቅልፍ ችግር፣ የስሜት መለዋወጥ፣ የብልት አካባቢ ድርቀት እና የጾታ ግንኙነት ላይ ምቾት ወይም ፍላጎት ማጣት የዚህ ተፈጥሮአዊ ለውጥ ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ለውጦች ተፈጥሯዊ ቢሆኑም ምልክቶቹ ሕይወትን ጥራት የሚያስተጓጉሉ ከሆነ ሃኪሞችን በማማከር ጤናማ ለውጥ ማድረግ ይቻላል።
በማረጥ ወቅት ጤናሽን ለመጠበቅ ምን ማድረግ ትችያለሽ?
🥗 1. የተመጣጠነ ምግብ
በዚህ ለውጥ ወቅት የአጥንት፣ የልብ እና የደም ሥር ጤናሽን መጠበቅ አስፈላጊ ስለሆነ በየቀኑ የተለያዩ አትክልቶችን፣ ፍራፍሬዎችን፣ እህሎችን፣ ጥራጥሬዎችን እና ጤናማ የፕሮቲን ምንጮችን ያካትቱ ምግቦችን ለመመገብ ሞክሪ።
ካልሲየም እና ቫይታሚን D ለአጥንት ጤና ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች ስለሆኑ ወተትና የወተት ተዋጽኦዎች፣ አረንጓዴ ቅጠላማ አትክልቶች እና በካልሲየም የበለጸጉ ምግቦች ጥሩ ምንጮች ናቸው።
🏋️♀️2. የአካል ብቃት እንቅስቃሴ
መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ክብደትሽን ለመቆጣጠር፣ የልብና የአጥንት ጤናሽን ለመጠበቅ፣ እንቅልፍሽን ለማሻሻል እና ስሜትሽን ለመቆጣጠር ይረዳሻል።
በሳምንት በአጠቃላይ ለ150 ደቂቃ ያህል መጠነኛ እንቅስቃሴ፣ ከጡንቻ ማጠናከሪያ ልምምዶች ጋር ለአብዛኛዎቹ ሴቶች ይመከራል። እንደ ፈጣን መራመድ፣ መዋኘት ወይም ብስክሌት መንዳት ያሉ እንቅስቃሴዎችንም መምረጥ ትችያለሽ።
🛌3. እንቅልፍ
የዚህ ወቅት ሆርሞናዊ ለውጦች እንቅልፍን ሊያስተጓጉሉ ይችላሉ። የመኝታ እና የመነሻ ሰዓትሽን ቋሚ ማድረግ፤ መኝታ ቤትሽን ቀዝቃዛና ምቹ ማድረግ እንዲሁም ከመኝታ በፊት ካፌይንን መቀነስ ጥሩ እንቅልፍ ለማግኘት ይረዱሻል።
🥵4. የሙቀት ስሜት
የሰውነት ሙቀት በድንገት መጨመር (Hot flashes) በማረጥ ወቅት የተለመደ ምልክት ነው። ቀላል ልብስ መልበስ፣ ክፍሉን ቀዝቃዛ ማድረግ እና በቂ ውሃ መጠጣት ይህን ለመቀነሽ ይረዱሻል።
በተጨማሪም ቡና፣ ቅመም ያላቸው ምግቦች፣ አልኮል ወይም ሌሎች የሙቀት ስሜትን የሚያባብሱ ነገሮችን በተቻለሽ መጠን መቀነስ ጠቃሚ ናቸው።
🦴5. የአጥንት ጤና
በማረጥ ወቅት የሚኖረው የኤስትሮጅን ሆርሞን መቀነስ የአጥንት ጥንካሬን ሊቀንስ እና የኦስቲዮፖሮሲስ አደጋን ሊጨምር ይችላል። ካልሲየምና ቫይታሚን D በበቂ መጠን ማግኘት፣ የክብደት መሸከም ልምምዶችን ማድረግ እና ማጨስን መተው የአጥንት ጤናን ለመጠበቅ ይረዳሉ።
💝6. የልብ ጤና
የደም ግፊትን፣ የደም ስኳርን እና ኮሌስትሮልን በሚመከረው ጊዜ በመመርመር ከለውጡ እና ከእድሜ መጨመር ጋር የተያያዙ የልብና የደም ሥር ችግሮችን መከላከል ይቻላል። ጤናማ ምግብ መመገብ፣ አዘውትሮ እንቅስቃሴ ማድረግ እና ማጨስን መተው አስፈላጊ ናቸው።
✍️7. የብልት ጤና
በማረጥ ወቅት የሚኖር የሆርሞን ለውጥ የብልት ድርቀትን፣ ማሳከክን ወይም በጾታ ግንኙነት ጊዜ ምቾት ማጣት ወይም ህመምን ሊያስከትል ይችላል። የውሃ መሠረት ያላቸው ማለስለሻ ሉብሪካንቶች (lubricants) ወይም ሌሎች አማራጮች ይህን ሊረዱ ይችላሉ። ጤና ባለሙያዎችን በመማማከር ምልክቶቹን መቀነስ ይቻላል።
🧘♀️8. የአእምሮ እና የስነ-ልቦና ጤና
ጭንቀት፣ ብስጭት ወይም የስሜት መለዋወጥ በማረጥ ወቅት ሊከሰቱ ሲችሉ ከቤተሰብና ከጓደኞች ጋር መነጋገር፣ መደበኛ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በቂ እንቅልፍ ማግኘት እና ለራስ የእረፍት ጊዜ መስጠት ይረዳሉ። የስሜት መቃወስ ከባድ ከሆነ የጤና ባለሙያን አነጋግሪ።
መቼ የጤና ባለሙያን ማማከር አለብሽ?
ማረጥ ተፈጥሯዊ ሂደት ቢሆንም ሁሉንም ምልክቶች በራስ መታገል አያስፈልግም። ምልክቶቹ የዕለት ተዕለት ሕይወትን፣ እንቅልፍን ወይም ግንኙነትሽን እያስተጓጎሉ ከሆነ የጤና ባለሙያን አማክሪ። በተለይም በማረጥ ወቅት ወይም በኋላ ማንኛውም የማህጸን ደም መፍሰስ ምልክት ካለ የጤና ባለሙያን በአፋጣኝ ማማከር ያስፈልጋል።
አስታውሺ! ማረጥ በሽታ ሳይሆን የሴቶች የሕይወት ተፈጥሯዊ ደረጃ ነው። ጤናማ አመጋገብ፣ መደበኛ እንቅስቃሴ፣ በቂ እንቅልፍ፣ የአጥንትና የልብ ጤና ክትትል እንዲሁም ተገቢ የሕክምና ምክር በዚህ የሕይወት ደረጃ ጤናሽን እንድትጠብቂ ይረዱሻል።



