የጭንቅላት ወባ (Cerebral Malaria and treatment)

Melat Geatchew
Sep 21, 2026
images   2026 09 21T165312.543

የጭንቅላት ወባ (Cerebral Malaria )

 

የወባ በሽታ በሀገራችን ስር የሰደደ ተላላፊ በሽታ ነው። 70 % በሚሆነው የኢትዮጵያ ክፍል የወባ ትንኝ ትገኛለች። ወባ የማያጠቃው ትንሽ አካባቢዎችን ብቻ ነበር። አሁን አሁን የወባ ስርጭት ባልተለመዱ የሀገራችን ቦታዎችም ጭምር ብቅ ብቅ እያለ ይገኛል። የአየር ንብረት ለውጥ ለዚህ እንደ ምክንያት ይጠቀሳል። 

የወባ በሽታ ከተላላፊ በሽታዎች በገዳይነቱ ወደር የሌለው ነው።በተለይ በህፃናት፣ ነብሰ ጡር እናቶችና አረጋዊያን ላይ ሲከሰት የገዳይነት ጉልበት ያገኛል።ወባ ገዳይ በሽታ ነው።ገዳይ በሽታ ነው ሲባል ሁሉንም ይገድላል፤ አይታከምም ማለት አይደለም።መታከም የሚችል ቢሆንም አዋጪው መፍትሔ ግን መከላከል ነው።የወባ ትንኝ ንክሻን በመከላከል፤የመራባት አቅሟን በማስቆም፣ ቅድመ መከላከል መድሐኒት በመውሰድ መከላከል ይቻላል።

ወባ ምንድን ነው?

ወባ በጥገኛ ተሕዋስያን ምክንያት የሚመጣ በሽታ ነው። የበሽታው ምልክቶች ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ማላብ፣ ራስ ምታት፣ የሰውነት መጓጎል፣ ማቅለሽለሽና ማስመለስ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ምልክቶቹ ከ48 እስከ 72 ሰዓት እየቆዩ በድጋሚ ይታያሉ፤ ይህን የሚወስነው ግለሰቡን ያጠቁት ተሕዋስያን ዓይነትና በበሽታው ተይዞ የቆየበት ጊዜ ነው።

የወባ በሽታ ምልክቶች

  •  ራስ ምታት፣ ድካም፣የጡንቻ ህመም፣ተኩሳት፣ማቅለሽለሽ፣ትውከት፣የደም ግፊት መቀነስ፣የጉበት እና ጣፊያ ማበጥ
  •  ብዙ ጊዜ የተለመዱ ምልክቶች - ( ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት እና ማንቀጥቀጥ)

የከባድ ወባ ዓይነት መገለጫዎች

  •  ራስን መሳት እና አለመንቃት
  •   ከፍተኛ ደም ማነስ
  •   የኩላሊት መድከም
  •   አይን ቢጫ መሆን
  •   የሚጥል በሸታ  ምልክት
  •   የሳንባ ላይ ዉሃ መቓጠር እና ለመተንፈስ መቸገር

 

ወባ አብዛኛውን የሰውነት ክፍል ያጠቃል። የከፋ ከሚሆንባቸው አንዱ አንጎልን ሲያጠቃ ነው። በተለምዶ የጭንቅላት ወባ(Cerebral malaria) ተብሎ ይጠራል።

የጭንቅላት ወባ (Cerebral malaria) በፈጣንነቱና በከባድነቱ የሚታወቅ፣ በPlasmodium falciparum በተባለ የነፍሳት ጥገኛ ተውሳክ አማካኝነት የሚከሰት ነው። ይህ በሽታ የሚከሰተው በወባ የተጠቁ በአንጎል ውስጥ ያሉ ትናንሽ ቀይ የደም ስሮች በወባ ተውሳክ ሲዘጉ የሚከሰት፣ ለሕይወት አስጊ እና ከባድ የሆነ የወባ ዓይነት ነው። በአብዛኛዉ በኢትዮጲያ ቆላ ቦታዎች የሚከሰት ሲሆን ከፍትኛ ጉዳት እና ብዙ ሞት የሚያስከትል ሲሆን ፋልሲፋረም (P. falciparum ) የሚከሰት ነው። 

 

የጭንቅላት ወባ በተለምዶ ከምናውቀው ወባ በተለየ መልኩ በቀጥታ ማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓትን (የአንጎል ክፍልን) የሚያጠቃ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄና አስቸኳይ የሕክምና ክትትልን ይሻል።

1. የጭንቅላት ወባ እንዴት ይከሰታል? 

የበሽታው መነሻ የሴት አኖፌልስ ወባ ንክሻ ነው። ትንኟ ተውሳኩን ወደ ደማችን ካስተላለፈች በኋላ፣ ተውሳኩ በጉበትና በቀይ የደም ሕዋሳት ውስጥ ይራባል። በጭንቅላት ወባ ወቅት ግን፣ እነዚህ የተበከሉ የደም ሕዋሳት እርስ በርሳቸው የመጣበቅ ባህሪ ስለሚያሳዩ በአንጎል ውስጥ ያሉ ጥቃቅን የደም ስሮችን ይዘጋሉ። ይህ ሲሆን ወደ አንጎል የሚሄደው የኦክስጅንና የደም ፍሰት ይቀንሳል፣ አንጎል ያብጣል፣ አልፎ ተርፎም ጥቃቅን የደም መፍሰስ ያጋጥማል።

2. የጭንቅላት ወባ ዋና ዋና ምልክቶች (Symptoms)

የጭንቅላት ወባ ምልክቶች በሽታው በሰውነት ውስጥ መሰራጨት ከጀመረ ከ24 እስከ 48 ሰዓታት ባለው ጊዜ ውስጥ በፍጥነት ሊባባሱ ይችላሉ።

  • የንቃተ ህሊና መዛባት ወይም ራስን መሳት፦ ታማሚው ከፍተኛ ግራ መጋባት፣ ከባድ እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት ወይም ሙሉ በሙሉ ራስን መሳት (Coma) ሊያሳይ ይችላል።
  • የሚጥል በሽታ ዓይነት መናድ (Seizures)፦ በተለይ በሕፃናት ላይ በተደጋጋሚ ሰውነትን የማንቀጥቀጥና የመናድ ምልክት ይታያል።
  • ከፍተኛ ትኩሳትና ራስ ምታት፦ ከ38° ሴ በላይ የሆነ የሰውነት ሙቀት መናር እና ሊቋቋሙት የማይችሉት ራስ ምታት።
  • ጽኑ ድካም እና የጡንቻዎች መዛል፦ ሙሉ በሙሉ ከአልጋ ለመነሳት መቸገር።
  • ሌሎች ምልክቶች፦ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ እና የአይን/የቆዳ ቢጫ (Jaundice)መሆን ናቸው።

3. እንዴት ይታወቃል? (Diagnosis)

ወደ ሕክምና ተቋም በሚሄዱበት ጊዜ ሐኪሞች በሽታውን ለመለየት የሚከተሉትን ምርመራዎች ያደርጋሉ፦

  • የደም ምርመራ (Blood Smear)፦ በአጉሊ መነጽር (Microscope) የወባ ተውሳክ በደም ውስጥ መኖሩን ማረጋገጫ ዋነኛ መንገድ ነው።
  • የፈጣን ወባ ምርመራ (RDT)፦ በደቂቃዎች ውስጥ ውጤት የሚሰጥ የምርመራ ዘዴ።
  • የጀርባ አጥንት ፈሳሽ ምርመራ (Lumbar Puncture)፦ ምልክቶቹ ከማጅራት ገትር (Meningitis) በሽታ ጋር ስለሚመሳሰሉ፣ እሱን ለመለየት የሚደረግ ምርመራ ነው።

4. ሕክምና እና መፍትሔዎች (Treatment)

የጭንቅላት ወባ በቤት ውስጥ በሚደረግ እንክብካቤ ወይም በክኒን መድኃኒቶች ሊድን አይችልም፤ አስቸኳይ የሆስፒታል አልጋና የጥብቅ  ክትትል (ICU) እርዳታ ያስፈልገዋል።

  • በደም ስር የሚሰጡ መድኃኒቶች፦ ዋነኛው እና ሕይወት አዳኙ ሕክምና በደም ስር የሚሰጥ አርቴሱኔት (IV Artesunate) ወይም ኩዊኒን (Quinine) የተባሉ ፀረ-ወባ መድኃኒቶች ናቸው።
  • የሰውነት መንቀጥቀጥ ወይንም መናድ  መቆጣጠሪያዎች፦ መናድንና መንቀጥቀጥን ለማቆም የሚሰጡ መድኃኒቶች።
  • ተጓዳኝ ሕክምናዎች፦ የታካሚውን የአተነፋፈስ ሥርዓት መደገፍ፣ የደም ስኳር መጠንን መቆጣጠር እና የደም ማነስ ካለ የደም ልገሳ ማድረግን ያጠቃልላል። በተጨማሪ መዳሀኒቶቹን በአግባቡ እንዲወስዱ ከማድረግ እና ከመምክር በተጨማሪ ተያያዠና የተወሳሰቡ ችግሮችን እንደ ደረጃቸዉ ትኩረት ሰጠቶ ማየት እና አፋጣኝ እርምጃ መዉሰድ ያስፈልጋል፡፡

5. የመከላከያ መንገዶች (Prevention)

በሽታው ከመከሰቱ በፊት አስቀድሞ መከላከል ምርጡ አማራጭ ነው፦

  • በፀረ-ተባይ የተበከሉ የአልጋ አጎበሮችን ወይንም ዛንዚራዎችን (Bed nets) አዘውትሮ መጠቀም። አጎበሩ፣ የተባይ ማጥፊያ የተረጨበት፣ ምንም ቀዳዳ የሌለው፣ በፍራሹ ዙሪያ የተጠቀጠቀ መሆን አለበት።
  • የመኖሪያ አካባቢን ንፁህ ማድረግ እና የቆሙ ውኃዎችን በማስወገድ የትንኝ መራቢያ ቦታዎችን ማጥፋት።
  • የሚቻል ከሆነ የወባ ትንኞች በብዛት ከሚገኙበት ጥሻ የሆነ አካባቢና ለትንኝ መራቢያነት አመቺ የሆኑ የታቆሩ ውኃዎች ካሉበት ቦታ መራቅ።
  • የወባ ምልክቶች (ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት) መታየት በጀመሩ በ24 ሰዓት ውስጥ ፈጣን የሕክምና ምርመራ በማድረግ በሽታው ወደ ጭንቅላት ወባ እንዳይቀየር መከላከል።በተለይም ልጆችና ነፍሰ ጡር ሴቶች ምልክቶቹ እየተባባሱ ከመሄዳቸው በፊት አፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ማግኘት አለባቸው። 
  • ወባ በተደጋጋሚ ወደሚከሰትበት ቦታ ለመሄድ የምናስብ ከሆነ ጉዞ ከመጀመራችን  በፊት ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት መሞከር። በአንድ አካባቢ ያለው የወባ ዓይነት በሌላ ቦታ ካለው ሊለይ ይችላል፤ ይህ ደግሞ ውጤታማ የሆነው መድኃኒት የትኛው እንደሆነ ለመወሰን ይረዳል።

 

Comments (0)