ክላስተር ራስ ምታት (Cluster headache)
- ክላስተር ራስ ምታት በጣም ከባድ ወይም ኃይለኛ ከሚባሉት የራስ ምታት አይነቶች ውስጥ አንዱ ነው። ይህ ራስ ምታት በተደጋጋሚ የሚከሰት፣ ለሳምንታት እስከ ወራት የሚቆይ፣ በመሃል ፋታ በመስጠት ለወራት ወይም ለአመታት ላይታይ ይችላል።
- ክላስተር ራስ ምታት በአንፃሩ ያልተለመደ የራስ ምታት አይነት ሲሆን ከአንድ በመቶ ያነሱ ሰዎችን ያጠቃል።
ክላስተር ራስ ምታት ምልክቶች ምንድናቸው?
- በድንገት ያለምንም ማስጠንቀቂያ ጀምሮ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በፍጥነት የሚጨምር ራስ ምታት
- አብዛኛውን ጊዜ ህመሙ አይን አካባቢ የሚጀምር ሲሆን አንድዳንድ ጊዜ ግን ከፊት፣ ከአንገት፣ ከጆሮ ወይም ከጭንቅላት ጎን አካባቢ ሊነሳ ይችላል።
- አብዛኛውን ጊዜ ምሽት ላይ ይከሰታል(ከ1 ወይም 2 የእንቅልፍ ሰዓታት በኋላ)
- ጭንቅላትን በአንድ ጎን ከፍሎ የሚከሰት ህመም፣ በተመሳሳይ ጎን በኩል
- የዓይን መቅላት፣ እንባ ማቅረር እና ብርሀን ለማየት መቸገር
- አፍንጫ መዘጋት ወይም ከአፍንጫ የሚወጣ ፈሳሽ መኖር እና
- ማላብ ሊኖር ይችላል።
- አለመረጋጋት፤ ሰዎች ህመሙ ሲነሳባቸው የራስ ቅላቸውን በፍጥነት ወደፊት እና ወደኋላ የማወዛወዝ ጠባይ ሊኖራቸው ይችላል፤ ይህ ጠባይ ክላስተር ራስ ምታት ከማይግሬን ራስ ምታት ለመለየት ጠቃሚ ሲሆን በተጨማሪም ማይግሬን አብዛኛውን ጊዜ ቅድመ ራስ ምታት ምልክቶች ይኖሩታል።
- ህመሙ በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሰት ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ከ 15 ደቂቃ እስከ 3 ሰዓታት ብቻ ይቆያል
- ህመሙ አብዛኛውን ጊዜ ልክ እንደጅማሬው በድንገት የሚያቆም ሲሆን ከጥቃቱ በኋላ አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የድካም ስሜት ይሰማቸዋል።
አጋላጭ ሁኔታዎች ምንድናቸው?
ምንም እንኳን የተረጋገጠ የክላስተር ራስ ምታት መንስኤ ባይኖርም የሃይፖታላምስ እጢ የሰዓት ቀመር የአሰራር ችግር ሲገጥመው ሊከሰት ይችላል ተብሎ ይገመታል። ከማይግሬን እና ቴንሽን ራስ ምታት በተለየ መልኩ ምግብ፣ የሆርሞን ለውጦች ወይም ውጥረት የክላስተር ራስ ምታት መንስኤ መሆን አይደሉም።
- ፆታ፤ ወንዶች ከሴቶች የበለጠ በዚህ ህመም የመያዝ ዕድላቸው ሰፊ ነው።
- ዕድሜ፤ በተለይም ከ20 50 ዕድሜ በአሉ ሰዎች ላይ ይከሰታል።
- አልኮሆል መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ
- በቤተሰብ ተመሳሳይ ህመም መኖር
ክላስተር ራስ ምታት ምርመራ
- የጤና ባለሙያው ምልክቶቹን በመረዳት ከአካላዊ የነርቭ ምርመራ በተጨማሪ የምስል ምርመራዎችን ሊያደርግ ይችላል።
አካላዊ የነርቭ ምርመራ
- የጤና ባለሙያው የነርቭ መዛባት ችግርን ለመለየት የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማል። ይህም የአንጎል ተግባርን፣ የስሜት ህዋሳትን፣ የነርቭ ቅፅበታዊ ምላሾችን እና የነርቭ ምርመራዎችን ያካትታል።
የምስል ምርመራዎች
- አስጊ የሆኑ የጤና እክሎችን ከክለስተር ራስ ምታት ለመለየት አንዳንድ ጊዜ የሚከተሉት የምሥል ምርመራዎች ሊታዘዙ ይችላሉ።
- ኤም አር አይ (MRI)
- ሲቲ ስካን(CT scan)
ሕክምናውስ ምንድነው?
- እሰከአሁን በተደረጉት ጥናቶች መሰረት ዘላቂ የሆነ የክላስተር ራስ ምታት ፈውስ የለም። ነገር ግን ህመሙን ለማስታገስ እና ለመከላከል የሚያግዙ የተለያዩ የሕክምና አማራጮች አሉ።
በፍጥነት የሚሰሩ የእፎይታ ሕክምናዎች
- የክላስተር ህመም በድንገት ጀምሮ በአፋጣኝ የማገገም ጠባይ ስለአለው እነዚህ ሕክምናዎች ውጤታማ ናቸው
- ኦክስጅን፤ ይህ ለአጭር ጊዜ በጭምብል የሚሰጥ ኦክስጅን ሲሆን በ15 ደቂቃ ውስጥ ጥሩ አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣል።
- መድኃኒቶች ትሪፕታን(Triptans) ይህ ለከባድ ክላስተር ራስ ምታት ውጤታማ መድኃኒት ሲሆን በተጨማሪም ማይግሬን ለማከም ይውላል።
- ሌሎች ኦክቴሮታይድ(Octerotide)፣ አንዳንድ ማደንዥዣዎች(Local anesthesia) እና ዳይሃይድሮኤርጎታሚን(Dihydroergotamine) የአሉ መድኃኒቶች ለአንዳንድ ሰዎች ህመሙን ለማከም ጥቅም ላይ ይውላሉ።
መከላከያ መድኃኒቶች፤ ለምሳሌ ካልሲየም ቻናል ብሎከርስ(Calcium channel blockers)፣ ኮርቶኮስቴሮይድስ(Corticosteroid)፣ ሊቲየም ካርቦኔት(Lithium carbonate)
- እነዚህ መድኃኒቶች በሽታው እዳይከሰት ለመከላከል የሚያገለግሉ ናቸው። አወሳሰዳቸው በበሽታው ድግግሞሽ እና ቆይታ ላይ የሚወሰን ሲሆን ህመሙ እየቀነሰ ሲሔድ መድኃኒቶቹም እየቆሙ ይሔዳሉ።
የቀዶ ጥገና ሕክምና
- ይህ አብዛኛውን ጊዜ በአደጉት አገራት የሚደረግ ሕክምና ሲሆን እጅግ ከባድ ራስ ምታት ከሆነ እና ሌሎች የሕክምና አማራጮች ውጤታማ ካልሆኑ በቀዶ ጥገና አማካኝነት የነርቭ ሕክምና ሊደረግ ይችላል።
በቤት ውስጥ የሚደረግ ሕክምና
- በቤት ውስጥ የሚከተሉትን በማድረግ የክላስተር ራስ ምታትህመምን መቀነስ ይቻላል።
- ወጥ የሆነ የእንቅልፍ መርሃግብር እዲኖር ማድረግ
- የአልኮሆልን መጠጥን ማስወገድ
- ሲጋራ አለማጨስ
- የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማዘውተር
- ህመሙ የሚያመጣውን ሁለንተናዊ ጫና ለመቋቋም የስነ ልቦና አማካሪ ማነጋገር
- ተደጋጋሚ የሆነ ራስ ምታት ሲከሰት የጤና ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል። በተጨማሪም ለሕክምና ይረዳ ዘንድ ህመሙ የተከሰተበትን ቀን፣ ቆይታ፣ የህመሙ ክብደት፣ የሚቀሰቅሱት እና የሚያሽሉት ነገሮች እና መድኃኒቶችን ማጤን ጠቃሚ ይሆናል።




