የማርገዝ እድልሽን በተፈጥሯዊ መንገድ ለመጨመር የሚረዱ መንገዶች!!

Elsabet Azezew
Nov 11, 2026
Joyful Pregnancy Test Celebration

                       የማርገዝ እድልሽን በተፈጥሯዊ መንገድ ለመጨመር የሚረዱ መንገዶች!! 

ልጅን በጉጉት ለሚጠባበቁ ጥንዶች ለማርገዝ የሚደረገው ጉዞ እጅግ አስደሳችም ፈታኝም ሊሆን ይችላል። ምንም እንኳን እርግዝና መቶ በመቶ እንዲፈጠር ዋስትና የሚሰጥ ዘዴ ባይኖርም፤ እነዚህ በማስረጃ የተደገፉ ቀላልና ተፈጥሯዊ ምክሮች ግን ወላጅ የመሆን ሕልምሽን ለማሳካት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋሉ። 

 

           1. ፎሊክ አሲድ መውሰድ ጀምሪ 

ፎሊክ አሲድ እንቁላል የሚለቀቅበትን ሂደትን (ovulation) በመደገፍ እና የፅንስ መፈጠርን (fertilization) በማገዝ የመራባት አቅምን ይደግፋል። ከዚህም ባሻገር፣ በፅንሱ ላይ የሚከሰቱ የአንጎልና የአከርካሪ አጥንት የአፈጣጠር ችግሮችን (Neural Tube Defects) በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል። 

ለማርገዝ ያሰበች ማንኛዋም ሴት እርግዝና ከመፈጠሩ ቢያንስ 3 ወራት ቀደም ብላ በቀን 400 ማይክሮግራም (400 mcg) ፎሊክ አሲድ እንድትወስድ ይመከራል። በተጨማሪም እንደ ቆስጣ፣ ባቄላ፣ ብርቱካን፣ እንጆሪ (Strawberry) እና ለውዝ ያሉ በፎሌት የበለጸጉ ምግቦችን በዕለት ተዕለት አመጋገብሽ ውስጥ አካትቺ። 

 

        2. እንቁላል በሚለቀቅበት ወቅት ግንኙነት አድርጊ (Fertile Window)

 

ለማርገዝ ከሚረዱ የተፈጥሮ መንገዶች መካከል አንዱና ዋነኛው እንቁላል ከእንቁልጢ ወደ ማህፀን ቱቦ በሚለቀቅበት ወቅት (ovulation) ግንኙነት ማድረግ ነው። እንቁላል ከመለቀቁ በፊት ባሉት አምስት ቀናት ውስጥ እና እንቁላል በሚለቀቅበት ዕለት ግንኙነት ማድረግ የማርገዝ እድልሽን በእጅጉ ያሰፋዋል። 

ይህ ሒደት የሚከሰተው በየወሩ እንቁልጢ ውስጥ የሚገኘው የእንቁላል ከረጢት በደንብ የጎለመሰውንና የበሰለውን እንቁላል ሲለቅ ነው።  እንቁላሉ ከተለቀቀ በኋላ በሕይወት የሚቆየው ከ12 እስከ 24 ሰዓታት ብቻ በመሆኑ፤ እንቁላል ከመውጣቱ ቀደም ብሎ ባሉት ቀናት ግንኙነት ማድረግ የወንድ የዘር ፍሬ በማኅፀን ቱቦ ውስጥ አስቀድሞ ተዘጋጅቶ እንዲጠብቀው በማድረግ የማርገዝ ዕድልን ይበልጥ ያጎለብተዋል። 

ታዲያ እንቁላል የሚለቀቅበትን ወቅት እንዴት ማወቅ ትችያለሽ? 

  • የወር አበባ ዑደትሽን ተከታተይ፦ እንቁላል አብዛኛውን ጊዜ የሚለቀቀው የሚቀጥለው የወር አበባ ከመምጣቱ ከ14 ቀናት ገደማ በፊት ነው። የወር አበባ ዑደታቸው መደበኛ ላልሆነ ሴቶች ቀኑ ሊለያይ ይችላል።
  • የማህፀን በር ፈሳሽሽን (Cervical Mucus) አስተውይ፦የጥሬ እንቁላል ነጭ ክፍልን የሚመስል፣ ጥርት ያለ፣ የሚያዳልጥ እና የሚለጠጥ ፈሳሽ መታየት እንቁላል ሊለቀቅ መቃረቡን ያመለክታል። 
  • የሰውነት መነሻ ሙቀትሽን (Basal Body Temperature) ለኪ፦ ጠዋት ከአልጋ ሳትነሺ የሚለካው የሰውነትሽ ሙቀት መጠነኛ ጭማሪ ካሳየ እንቁላል መለቀቁን ይጠቁምሻል። 
  • የእንቁላል መለቀቅን የሚያሳዩ መመርመሪያ ኪቶችን (Ovulation Test Kits) ተጠቀሚ፦ የሐኪም ማዘዣ ሳያስፈልግ ከፋርማሲ የሚገዙት እነዚህ ኪቶች በሽንት ውስጥ የሚገኘውን የLH ሆርሞን መጠን በመለካት እንቁላል የሚለቀቅበትን ቀን በትክክል ያሳውቃሉ። 

የወር አበባ ዑደትሽን በሚገባ መረዳትና እነዚህን ምልክቶች ለይተሽ ማወቅ፣ እርግዝና የመፈጠር ዕድሉ ከፍተኛ የሚሆንባቸውን ቀናት (Fertile Window) ለይተሽ ግንኙነት የምታደርጊበትን ጊዜ በተሻለ ሁኔታ እንድታስተካክይ ይረዳሻል። 

 

       3. መደበኛ የግብረ-ስጋ ግንኙነት ይኑርሽ 

 

በሳምንት ከ2 እስከ 3 ጊዜ መደበኛ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ማድረግ የማርገዝ ዕድልሽን በእጅጉ ከፍ ያደርጋል። የወንድ የዘር ፍሬ (Sperm) በሴት የመራቢያ አካል ውስጥ እስከ 5 ቀናት ድረስ በሕይወት መቆየት የሚችል በመሆኑ አዘውትሮ ግንኙነት ማድረግ እንቁላል በሚለቀቅበት ቅጽበት የዘር ፍሬው አስቀድሞ በማኅፀን ቱቦ ውስጥ ተዘጋጅቶ እንዲጠብቅ ያስችለዋል። 

ይህ በተለይ ዑደታቸው ላልተስተካከለ ሴቶች ወሳኝ መፍትሔ ነው፤ በእነዚህ ሁኔታዎች እንቁላል የሚወጣበትን ቀን በትክክል መተንበይ ስለሚከብድ መደበኛ ግንኙነት ማድረግ አመቺው ለም ወቅት ሳያመልጣቸው ለመጠቀም ዋስትና ይሰጣል። 

 

        4. ከግንኙነት በኋላ ለ10–15 ደቂቃ ከአልጋ ሳትነሺ ጋደም በይ 

 

ይህም የወንዱ የዘር ፍሬ ወደ ማህፀንሽ ውስጠኛ ክፍል በቀላሉ ዋኝቶ እንዲገባ እና ወደ እንቁላል የሚደርሱት የዘር ፍሬዎች ቁጥር እንዲጨምር ያግዛል።

ከግንኙነት በኋላ ወዲያውኑ መነሳት የተወሰነው ፈሳሽ እንዲወጣ ሊያደርግ ስለሚችል በጀርባ ጋደም ብሎ ማረፉ ይመረጣል፤ ሆኖም እግርን ግድግዳ ላይ መስቀል አያስፈልግም በጀርባ ማረፍ ብቻ በቂ ነው። 

 

        5. ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ተከተይ

 

እነዚህን ልማዶች ባልና ሚስት በጋራ ሲተገብሯቸው የመራቢያ አካላትን ጤና በመደገፍ የማርገዝ ውጤታማነትን የላቀ ያደርጋሉ፦ 

  • የተመጣጠነ ምግብ ተመገቢ 

አትክልቶችን፣ ፍራፍሬዎችን፣ ያልተፈተጉ እህሎችን፣ ጥራጥሬዎችን፣ በፕሮቲን የበለጸጉ ምግቦችንና ጤናማ ቅባቶችን በአመጋገብሽ ውስጥ አካትቺ። 

  • አዘውትረሽ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርጊ 

እንደ ፈጣን የእግር ጉዞ ያሉ መጠነኛ እንቅስቃሴዎችን አዘውትሪ፤ የወር አበባ ዑደትሽን ሊያዛባ ከሚችል ከልክ ያለፈ ከባድ ስፖርት ግን ተቆጠቢ። 

  • ጤናማ የሰውነት ክብደትን ጠብቂ 

የሰውነት ክብደት ከመጠን በላይ ማነስም ሆነ መጨመር በእንቁላል መለቀቅ ሒደትና በሆርሞን ሚዛን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። በተጨማሪም ከመጠን ያለፈ ውፍረት በወንዶች የዘር ፍሬ (ስፐርም) ጥራት ላይ ጉዳት ያስከትላል። 

 

       6. ጭንቀትን ቀንሺ፤ በቂ እንቅልፍ አግኚ

 

ለማርገዝ የሚደረገው ጥረት አድካሚና የሚያስጨንቅ ሊሆን ይችላል። ምንም እንኳ ጭንቀት በቀጥታ ለመካንነት ባይዳርግም የማያቋርጥ ውጥረት ግን የሆርሞን ሥርዓትን በማወክ የወር አበባሽን ሊያዛባና አጠቃላይ ጤናሽን ሊጎዳ ይችላል። 

በመሆኑም በቂ እንቅልፍ ለመተኛት፣ ዘና ለማለትና የሚያስደስቱሽን ተግባራት ለማከናወን ጊዜ መድቢ። 

 

       7. የመውለድ አቅምን (Fertility) ሊጎዱ ከሚችሉ ልማዶች ተቆጠቢ

 

አንዳንድ የዕለት ተዕለት ልማዶች የመራቢያ ሥርዓትሽን ጤና ስለሚጎዱ የማርገዝ ዕድልሽን ከፍ ለማድረግ የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች አድርጊ ፦ 

  • በቀን ከ1–2 ሲኒ በላይ ቡና አትጠጪ

በቀን ከ1 እስከ 2 ሲኒ በላይ ቡና መጠጣት እርግዝና ለመፈጠር የሚወስደውን ጊዜ ከማራዘሙም ባሻገር የሆርሞን ሚዛንን ሊያዛባና በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት የሚከሰት የፅንስ መጨንገፍ ሥጋትን ሊያባብስ ይችላል። በወንዶች በኩልም ከመጠን ያለፈ የካፌይን መጠን የስፐርም ብዛትንና የመንቀሳቀስ አቅምን ሊጎዳ ይችላል። 

  • አልኮልና ሲጋራን ከመጠቀም ተቆጠቢ

ሁለቱም የእንቁላልንም ሆነ የወንድ የዘር ፍሬን ጥራት ስለሚያበላሹ ለእርግዝና መሰናክል ይሆናሉ። 

  • አጋርሽ ከመጠን ያለፈ ሙቀት (ሳውና እና ሙቅ ገንዳ) እንዲርቅ አድርጊ 

የወንድ የዘር ፍሬ ጥራትና ምርት በከፍተኛ ሙቀት በቀላሉ ይጎዳል። ስለዚህ ሙቅ ውሃ በተሞላ ገንዳ (Hot tubs) ውስጥ ለረጅም ጊዜ ከመቆየትና ሳውናን (Sauna) አዘውትሮ ከመጠቀም መቆጠብ ይኖርበታል። 

 

           የሕክምና ባለሙያ ማማከር ያለብሽ መቼ ነው? 

አንቺና አጋርሽ ጤነኛ ሆናችሁ እንኳ እርግዝና ወዲያውኑ ላይፈጠር ይችላል። ይሁን እንጂ የሚከተሉት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ የሕክምና ባለሙያ ማከር ይመከራል ፦  

  • ዕድሜሽ ከ35 ዓመት በታች ሆኖ ለ1 ዓመት ያህል መደበኛ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት እያደረጋችሁ እርግዝና ካልተፈጠረ
  • ዕድሜሽ 35 ዓመት እና ከዚያ በላይ ሆኖ ለ6 ወራት ያህል ጥረት አድርጋችሁ ካልተሳካ 

ሆኖም የወር አበባ መዛባት ፣ ከባድ የወር አበባ ሕመም ወይም የታወቀ የመራቢያ አካላት እክል ካለብሽ ጊዜ ሳታጠፊ ወዲያውኑ መመርመር ይኖርብሻል። 

Comments (0)