Learning materials for your health  Learn

የአስም በሽታ

  • September 7, 2021
  • የጤና እክሎች

የአስም በሽታ እየተደጋገመ የሚመጣ፣ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ፣ የመተንፈሻ ቱቦ እና የሳምባ ሕመም ነው።  በሽታው የአየር ቱቦዎችን በማጥበብና በማስቆጣት መተንፈስን ከባድ ያደርገዋል፡፡ 

የአስም በሽታ በበለፀጉት አገራት የበለጠ ቢከሠትም፤ አሁን አሁን ግን በታዳጊ አገሮችም እየጨመረ ይገኛል።

በዓለማችን 10 - 12% የሚሆኑት ጎልማሳዎችና እና 15% የሚሆኑት ሕፃናት  በዚህ በሽታ ይጠቃሉ። ወንዶች ሕፃናት ከሴት ሕፃናት የበለጠ ተጋላጭ ናቸው። በወጣቶች ላይ ግን ሁለቱም እኩል ተጋላጭ ሲሆኑ፤ ዕድሜያቸው ከ 40 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ይጠቃሉ። 

ለአስም በሽታ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

  • በቤተሰብ የአስም ሕመም ከአለ፤
  • በልጆች ላይ  የቆዳ ወይም ማንኛውም ዓይነት የመተንፈሻ አካላት አለርጂ ከአለ ፤
  • ታማሚው  አዋቂ ከሆነ ደግሞ በልጅነት ጊዜ ማንኛውም ዓይነት የአለርጂ ችግር ከነበረ፤
  • የመተንፈሻ አካላት አለርጂ ከነበረ፤
  • ከመጠን ያለፈ ውፍረት
  • ሲጋራ ማጨስ ወይም ተገብሮ ማጨስ (passive smoking)
  • የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን

የአስም በሽታ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

የአስም ምልክቶች ቀላል ወይም ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ። ምንም እንኳን አልፎ አልፎ ቢሆንም የአስም ምልክቶች በድንገት ጀምረው እስከ ሞት ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡

  • በሚተነፍሱበት ወቅት ሲር ሲር የሚል ድምፅ ማሰማት፤
  • ሳል (በተለይም ምሽት ላይ)
  • በደረት አካባቢ የመጨነቅ ስሜት 
  • ትንፋሽ ማጠር

ምልክቶቹ በየቀኑ፣ በየሳምንቱ ወይም ከዚህም ባነሰ ጊዜ ሊከሠቱ ይችላሉ፡፡ 

የአስም በሽታ ምርመራዎች

ከላይ የተጠቀሱት  ምልክቶች  እንዳሉ ሆነው በተጨማሪም ሪስፓይሮሜትር (የመተንፈሻ መለኪያ) ምርመራ ይደረጋል፡፡ ይህም የሳምባን የመተንፈስ ዐቅም የሚለካ እና የአለርጂ ችግር ከአለም  ምርመራ የሚደረግበት ነው፡፡።

የአስም በሽታ እንዴት ይታከማል?

ሕክምናው ከሥር የተጠቀሱትን ሁለት ነገሮች መሠረት ያደረገ ይሆናል።

  • ምልክቶቹ  በየስንት ጊዜው ይከሠታሉ?
  • ምን ያህል ከባድ ናቸው?
  1. የፈጣን - እፎይታ መድኃኒቶች (quick relief medicines)፡- እነዚህ በአፍ የሚነፉ መድኃኒቶች የአስም ምልክቶች በሚከሠቱበት ጊዜ ሁሉ ይወሰዳሉ። መድኃኒቶቹ ለመሥራት የሚወስድባቸው  ጊዜ ከ 5 - 15 ደቂቃ ሲሆን፤ በፍጥነት ፋታ በመስጠት ምልክቶቹን የሚያስታግሱ ናቸው።

  2. የረጅም ጊዜ ማስታገሻ (long term controllers) መድኃኒቶች፡- እነዚህ መድኃኒቶች ቶሎ ለውጥ ባያሳዩም የአስም በሽታን በመቆጣጠር ወደፊት ምልክቶቹ እንዳይከሠቱ ይከላከላሉ። ስለዚህ መድኃኒቱን ሳያቋርጡ መውሰድ  ያስፈልጋል። በሳምንት ውስጥ ከ ሁለት ጊዜ በላይ የአስም በሽታ ምልክቶች የሚታዩባቸው ሰዎች፤ በየቀኑ አንድ ወይም ሁለት ጊዜ የመቆጣጠሪያ መድኃኒት መጠቀም ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

በአጠቃላይ የአስምን በሽታ ለመቆጣጠር የሚከተሉትን መተግበር ያስፈልጋል።

  • በሕክምና ተቋም ውስጥ በመደበኛነት ክትትል ማድረግ
  • ክትትሉ በየ1 - 6 ወር ሊሆን ይችላል፡፡ በክትትሉ ወቅትም የጤና ባለሙያው ፣ ስለመድኃኒቶቹና አጠቃቀማቸው በሚገባ ያስረዳል፡፡ ማለትም  የአስም ታማሚዎች በቤት ውስጥ በየቀኑ የሚጠቀሙባቸው የትኞቹ መድኃኒቶች እንደሆኑ፣ምልክቶች እየባሱ ከሄዱ የትኞቹን መድኃኒቶች መውሰድ እንደአለባቸው፣ በሽታውን የሚያስነሡትን ሁኔታዎች ስለመቆጣጠር ጨምሮ ትምህርት ይሰጣል። 
  • በተጨማሪ በሕመሙ  ምልክቶች እና በሳምባ ምርመራ ውጤቶች መሠረት መድኃኒቶች ይስተካከላሉ።

የአስም ሕመምተኞች  ፈጣን የሕክምና ርዳታ የሚስፈልጋቸው መቼ ነው?

ምልክቶቹ በድንገት ከተከሠቱና በጣም የከፉ ከሆኑ (acute exacerbation) በመጀመሪያ ፈጣን የርዳታ መድኃኒትን ይጠቀሙ። መድኃኒቱን ከተጠቀሙ  በኋላ  የሕመሙ ምልክቶች በአንድ ሰዓት ውስጥ  ካልተሻሻሉ  ወይም  እየተባባሱ  ከሄዱ ፈጥነው ወደ ጤና ተቋም በመሔድ ርዳታ ማግኘት ያስፈልጋል።

የአስም በሽታ ምልክቶችን መከላከል ይቻላል?

  • የአስም በሽታን ከሚቀሰቅሱት ነገሮች መራቅ።  ምንም እንኳን የተለመዱ  የአስም በሽታ ቀስቃሾች ቢኖሩም፤ ነገር ግን የእርስዎ የአስም ሕመም ቀስቃሽ መንሥኤዎች የተለዩ ሊሆኑ ስለሚችሉ ለይቶ ማውቅና ማስወገድ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ፦ 
    • የኣቧራ ብናኝ፣ ሲጋራ ማጨስ ወይም ከሚጨሱባቸው አካባቢዎች መራቅ 
    • ጉንፋን፣ ጭንቀት እና ቅዝቃዜ ማስወገድ 
    • ከቤት እንስሳት (ውሻ፣ ድመት) መራቅ
    • አንዳንድ የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን (NSAID) ከመውሰድዎ በፊት ሐኪምዎን ማማከር
  • የአካል ብቃት እንቅስቃሴ -  ምንም እንኳን ለአንዳንድ የአስም በሽተኞች ቀስቃሽ ሊሆን ቢችልም ለሌሎች ግን ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከመደረጉ በፊት ፈጣን የእፎይታ መድኃኒት በተጨማሪ መጠን መውሰድ ሊያስፈልግ ይችላል።

ስለዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ማስወገድ ወይም መከላከል፣ ሲጋራ ማጨስ ማቆም፣ ወይም ከሚጨሱባቸው ቦታዎችም መራቅ፣ በቀዝቃዛ ወቅቶች  በአፍንጫ  እና በአፍ ላይ  ሻርፕ ወይም ጭምብል ማድረግ፣ በሐኪም የታዘዘልዎትን መድኃኒት በአግባቡ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

የአስም በሽታን  በተገቢው ተቆጣጥረነዋል የምንለው መቼ ነው?

  • የአስም በሽታ ምልክቶች በቀን ከሆነ የሚከሠቱት  በሳምንት ከሁለት ጊዜ በላይ መብለጥ የለባቸውም። 
  • በአስም በሽታ ምክንያት በምሽት  ከእንቅልፍ የምንነቃው በወር  ከሁለት  ጊዜ  ካልበለጠ እና
  • የተለመደውን እንቅስቃሴ ያለምንም እንከን ማከናወን  ስንችል፤ የአስም በሽታን  በተገቢው ተቆጣጥረነዋል ማለት እንችላለን ።

የኮቪድ-19 በሽታ እና አስም

አስም በሽታ ያለባቸው ሰዎች ከሌላው ሰው በበለጠ መልኩ በኮሮና ቫይረስ የመያዝ እና ከባድ የኮሮና ምልክቶች የማሳየት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ 

ስለዚህ የአስም በሽታ ከአለብዎ ከሌላው ሰው በተለየ ጥንቃቄና የመከላከያ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል። 

አስም ለአለባቸው ሰዎች የኮሮናን ቫይረስ ለመከላከል የሚያስፈልጉ ቅድመ ጥንቃቄዎች

  • በተቻለ መጠን በቤት ውስጥ መቆየት፡፡ 

  •  ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ፡፡

  • ጭምብል ማድረግ - ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ጭምብሎች አስምን አያባብሱም፡፡

  • እጅዎን በሳሙና መታጠብ ወይም ሳኒታይዘር መጠቀም፡፡ 

  • የአስም መድኃኒቶችን በአግባቡ መውሰድ፡፡

  • የአስም በሽታዎን የሚያባብሱ ነገሮችን ለይቶ ማወቅ እና በተቻለ መጠን መጠንቀቅ፡፡

  • ምንጣፎችን እና ወለሎችን በተደጋጋሚ ማጽዳት፤ መረጃው እንደሚያመለክተው የኮሮና ቫይረስን እንደ ፕላስቲክ እና ብረት ባሉ ወለሎች ላይ እስከ 72 ሰዓታት ድረስ ሊቆይ ይችላል፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን ቅድመ ጥንቃቄዎች በአግባቡ በመተግበር የኮሮና ቫይረስን መከላከል ይቻላል፡፡

ሳል፣ ትኩሳት፣ የደረት ሕመም እና የአየር እጥረት የመሳሰሉትን የኮቪድ-19 በሽታ ምልክቶች ከአዩ ወዲያውኑ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን ሕክምና ማግኘት አለብዎት፡፡ በሙያው የተካኑ ሐኪሞችን ለማግኘት ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ

Share the post

scroll top