Learning materials for your health  Learn

የድባቴ ህመም

  • March 25, 2022
  • የጤና እክሎች

 

የድባቴ ሕመም (Major Depressive Disorder)

 

ድባቴ ምንድን ነው?

 

ድባቴ ከተከታታይ ሁለት ሳምንታት በላይ የሚቆይ የመደበር፣ ደስታ የማጣት ወይም የመነጫነጭ ሕመም ነው። ከታች በዝርዝር የሚብራሩ ሌሎች ተጨማሪ መገለጫ ምልክቶች አሉት፡፡ ሕመሙ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን የሚያስተጓጉል መሆኑ ከተለመደው ጊዜያዊ የመነጫነጭ ወይም የድብርት ስሜት ይለየዋል።

 

ከዓለም ሕዝብ ውስጥ ከ 10 - 15% የሚሆነው ቢያንስ በሕይወቱ አንድ ጊዜ የድባቴ ሕመም ይይዘዋል። በኢትዮጵያ ድባቴ ከ 9% በላይ ሕዝብ እንደሚያጠቃ ጥናቶች ያሳያሉ።

 

ለድባቴ ሕመም አጋላጭ ሁኔታዎች ምን ምንድን ናቸው?

 

ሥነ ሕይወታዊ አጋላጭ ሁኔታዎች

  • ከዚህ በፊት በድባቴ ሕመም ተይዘው የሚያውቁ ከሆነ

  • በበሽታው የተያዘ የቤተሰብ አባል ከአለ

  • የመጠጥ ወይም አደንዛዥ ዕፅ ሱስ ከአለ

  • አካላዊ የአንጎል ሕመም ከአለ

 

ሥነ ልቦናዊ አጋላጭ ሁኔታዎች

  • በልጅነት ዕድሜ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ ወይም ጾታዊ ጥቃት ከአጋጠመ

  • ነገሮችን በአሉታዊ መንገዶች የመመልከት ዝንባሌዎች ከአሉ

  • ለራስ ዝቅ ያለ ግምት የሚሰጡ ከሆነ (በራስ መተማመን ማጣት)

 

ማኅበራዊ አጋላጭ ሁኔታዎች

  • ፍቺ እና ከጋብቻ ጋር የተያያዙ ችግሮች ከአሉ

  • በልጅነት ጊዜ የወላጅ ሞት ከነበረ

  • የትዳር አጋርን በሞት ማጣት ከአለ

ለድባቴ ሕመም የሚኖረው ተጋላጭነት ከፍ ያለ ይሆናል።
 

የድባቴ ሕመም ምልክቶች ምን ምንድን ናቸው?

 

የድባቴ ሕመም የተለያዩ ምልክቶች አሉት። አንዳንድ ጊዜ የሚቃረኑ የሚመስሉ ምልክቶችንም ጭምር ሊያሳይ ይችላል። ለምሳሌ፦ ድባቴ የምግብ ፍላጎትን ሊጨምርም ሊቀንስም ይችላል።

 

በዋነኛነት የድባቴ ሕመምተኞች ከሚከተሉት ሁለት ምልክቶች ውስጥ ቢያንስ አንዱ ይታይባቸዋል፡፡

 

  1. ከዚህ በፊት ማድረግ የሚወዱትን ነገር ማድረግ አያስደስታቸውም። ለምሳሌ ኳስ ጨዋታ ማየት ይወድ የነበረ ሰው በዚህ ሕመም ሲያዝ ኳስ ጨዋታ ማየት ሊጠላ ይችላል።

  2. በቀን ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ በሐዘን፣ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ያሳልፋሉ። ይህም ስሜት በየቀኑ ሊባል ለሚችል ጊዜ፣ ከቀኑም በአብዛኛው ሰዓት ሊያጋጥም ይችላል።

 

ከእነዚህ ምልክቶች በተጨማሪም

 

  • ምክንያት የሌለው ክብደት መቀነስ ወይም መጨመር

  • ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ብዙ ሰዓት መተኛት ወይም እንቅልፍ ማጣት

  • የድካም ወይም ኃይል የማጣት ስሜት

  • የጥፋተኝነት ስሜት ወይም ለራስ ዋጋ አለመስጠት

  • ነገሮችን በቀላሉ የመርሳት ወይም ግራ የመጋባት ስሜት ሊኖር ይችላል

  • ከወትሮው በተለየ በዝግታ ወይም ድምፅን ቀንሶ ማውራት

  • ዕረፍት ማጣት

  • ራስን የማጥፋት ሐሳብ ሊኖር ይችላል።

 

አንድ ሰው እነዚህን ምልክቶች ቢያንስ ለሁለት ሳምንታት በየቀኑ (በቀን ውስጥ ለብዙ ሰዓታት) ከአሳየ በድባቴ በሽታ ተጠቅቷል ማለት እንችላለን። ነገር ግን በሽታውን ለማረጋገጥ፣ ሌሎች ተያያዥ በሽታዎችን ለመለየትና ሕክምናውን ለመጀመር ከአእምሮ ሐኪም ጋር መነጋገር ያስፈልጋል።


 

ድባቴን ከድብርት የሚለየው በምንድን ነው?

 

ድብርት እና ሐዘን በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሠት የሚችል የስሜት ዓይነት ሲሆን፤ ብዙውን ጊዜ የቀን ተቀን ሕይወታችንን አያስተጓጉልም። ይህም ማለት ሥራ መሥራት፣ መማር፣ ከጓደኛና ከቤተሰብ ጋር ጊዜ ማሳለፍን አይከለክልም። በአንጻሩ ድባቴ በቀን ተቀን ሕይወታችን ላይ ጫና ያሳድራል። ለምሳሌ፡ ሠራተኛው ሥራ መሥራት፣ ተማሪው ትምህርቱን መከታተል ሊያቅተው ይችላል።

 

የድባቴ ሕመም በአለባቸው ሰዎች አንጎል ውስጥ የሚገኙ መልእክት አስተላላፊ ኬሚካሎች ከሌላው ጤነኛ ሰው የተለዩ መሆናቸውን ሳይንሳዊ ጥናቶች ያሳያሉ።

 

የድባቴ ሕመም እንዴት ይታከማል?

 

ድባቴ የአለባቸው ሰዎች ከሚከተሉት ሕክምናዎች ውስጥ አንዱን ወይም ከአንድ በላይ ሊጀምሩ ይችላሉ።

  1. የፀረ ድባቴ መድኃኒቶች

  2. የንግግር ሕክምና (ከአእምሮ ሐኪም፣ ከሥነ ልቦና ባለሙያ፣ ከሌሎች የሠለጠኑ የጤና ባለሞያዎች ጋር)

  3. ማኅበራዊ ድጋፍ ማድረግ

 

የፀረ ድባቴ መድኃኒቶች

 

በኪኒን ከሚሰጡ ሕክምናዎች ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉት ፍሎክሲቲን (fluoxetine)፣ አሚትሪፕቲሊን (Amitriptyline)፣ ሰርትራሊን (Sertraline) እና ኢሚፕራሚን (Imipramine) ናቸው፡፡ እነዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የሆኑ የድባቴ፣ የጭንቀት እና ሌሎች የአእምሮ እክሎችን ለማከም የሚውሉ ናቸው።

 

የንግግር ሕክምና

 

ድባቴን ለማከም የሚያገለግሉ የተለዩ የሥነ ልቦና ሕክምና ዓይነቶች አሉ፡፡ እያንዳንዳቸው በራሳቸው መንገድ ይሠራሉ፡፡ ነገር ግን ሁሉም የድባቴን ምልክቶች ለማሻሻል እንደሚረዱ ሳይንሳዊ ጥናቶች ያሳያሉ። ሁሉም የንግግር ሕክምናዎች የየራሳቸው የተጠና ዘዴ አላቸው። በአብዛኛው ስሜትን፣ አስተሳሰብን፣ ድርጊትን ወይም ማኅበራዊ መስተጋብርን በመመርመር እና በማሻሻል የድባቴ ሕመም ምልክቶችን ያክማሉ። 

በኢትዮጵያ በብዛት ኮግኒቲቭ - ቢሄቪየራል የንግግር ሕክምና (Cognitive-behavioral therapy) እና የእርስ በእርስ ግንኙነቶች ላይ ያተኮረ የንግግር ሕክምና (Interpersonal psychotherapy) ጥቅም ላይ ይውላሉ።



 

የንግግር ሕክምና አካል ሆኖ የሚሰጥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ 

 

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የመንፈስ ጭንቀትን ያቃልላል። በሳምንት ከሦስት እስከ አምስት ቀናት ከ 45 እስከ 60 ደቂቃዎች ማንኛውንም ዓይነት የአካል እንቅስቃሴ (እንደ መራመድ፣ መሮጥ፣ ወይም ብስክሌት መንዳት) ይመከራል።



 

Share the post

scroll top